የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ [ሸንጎ] ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ

ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ በፍራንክፈርት ተካሄደ

 

በጀርመን የኢ/ዊያን የትብብርና የውይይት መድረክ በሀገራችን ውቅታዊና አንገብጋቢ  ችግሮች ዙርያ ከኢ/ዊያን ወገኖች ጋር ቅዳሜ ሐምሌ 09.07.2016 በፍራንክፈርት ከተማ የተሳካ  ሕዝባዊ ስብሰባ አካሂደዋል።
ስብሰባው የተጀመረው የውይይትና የትብብር መድረኩ ባለፈው ዓመት ስላከናወናቸው አበይት ተግባራትን አስመልክቶ በውይይትና የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ አማካይነት የቀረበውን አጭር የስራ ሪፖርት በማዳመጥ ነበር።
ተሰብሳብዎችን ያወያዩት በአሜርካን ሀገር በሰሜን ካሮላይና ሴንትራል ዩኒቨርስቲ የስነጥበብ ማእከል ፕሮፌሰርና የሸንጎው ከፍተኛ አመራር ኮሚቴ አባል የሆኑት ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር አቻሜየለህ ደበላ ናቸው።
ፕሮፌሰር አቻሜየለህ ደበላ የሸንጎውን መሰረታዊ ዓላማና ደንብ አባላትን ሸንጎው እስከዛሬ ያከናወናቸውን ተግባራት ለወደፊቱ ሊተገብራቸው ያሰባቸውን ዝርዝር  እቅዶችን በአጠቃላይ በሀገራችን ፖለቲካ  የሸንጎውን ድርሻና ሚና በስፋትና በጥልቀት በመዘርዘር ዛሬ በሀገራችን ተክስተው ለሚገኙት ዘርፌ ብዙ ችግሮች ዋናው ተጠያቂና የችግሩ መንስዔ የሆነው በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ገዥ የወያኔ ኢሕአዲግ መንግስት ከሚያራምደው ዘረኛ ፖሊሲና በጎሳ ከፋፍሎ መግዛት ስርዓት የተነሳ መሆኑን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመነሳት በዝርዝር በመተንተን በማስረጃ በተደገፉ ተግባራት የሚታዩትን ችግሮች በሰፊው በማብራራት ኣአስረድተዋል።

ከወያኔው መንግስት ካስከተለው ችግሮችም ጎን እኛም በተቃዋሚ ጎራ የቆምነው ክፍሎች በአንድነት በመተባበር ለመታገል አለመቻላችን ደግሞ ችግራችንን የበለጠ ለማባባስና ውስብስብ በማድረጉ ረገድ የራሳችንን አፍራሻ አስተዋጽኦ ማበርከታችንን ፕሮፌሰር አቻሜየለህ ደበላ እንዲዚሁ ለተሰብሳቢዎቹ አስረድተዋል፡፡
ፕሮፌሰር አቻሜየለህ፣ ሰለ ህውሃት/ኢሕአዲግ ከፋፋይና አግላይ ስርዓት ሲገልጹም የሚከተሉትን ነጥቦች ዘርዝረዋል፣
የስርዓቱ እንዳለ መቀጠል ለሀገር አንድነትም ሆነ ለህዝባችን ሰላም እጅግ ሰፊ አደጋን ይጋብዛል በመሆኑም የስርዓቱ መቀየር ለነገ የማይባል አሁን የግድ መለወጥ ያለበት ስርዓት ነው ይላሉ፡፡
በሀገራችን ውስጥ የተለያዩ ወገኖቻችን የተለያዩ ብሶት እንዳለባቸው ግልጽ ነው፣ለወደፊት ለሚመሰረተው አዲሱ ስርዓት ኢትዮጵያዊያን የሀገራችንን ችግሮች በሀገራችን አንድነት ጥላ ስር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መነጋገር መወያየት መደራደር መስማማትና ለዚህም መስራት ይኖርብናል፡፡

አያይዘውም ሲያብራሩ በየምክናያቱ ሀገራችንን ለመበታተን የሚደረገውን እንቅስቃሴ ሁሉ ያለምንም ማወላወል ልንቃወመው ይገባናል አሁን በህዝባችን ላይ የተጫነው ስርዓት ተወግዶ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋው የተከበረበት ማንነቱ የተከበረበት የህግ የበላይ የሰፈነበት ህገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት አጣዳፊ ተግባራችንም እንደሆነ አሳስበዋል።
በክብር እንግድነት ተጋብዘው የሰብሰባውን ታዳሚዎች ያወያዩት ፕሮፌሰር አቻሜየለህ ከሸንጎው እይታ አኳያም ሲገልጹ አግላይ ያልሆነ የተቃዋሚ ሰፊ ግንባር/ትብብር መመስረት አስፈላጊነቱን፣ በተበታተነ መልክ የሚካሄደው ትግል ለየብቻ በሚደረግበት ጥቃት ሰላባ ከመሆም አልፎ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብሎ መገመት
ያዳግታል፡፡በእርግጥም ለሀገራችን ብሩህ ተስፋ ሰንቀው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ይህንን ተገንዝበው መላን የተላበሰ የተባበረ
ትግል ማድረግ እጅግ አስላጊ ስለመሆኑና ለዚህም ተግባራዊነት ደግሞ ሸንጎው ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። የታቃዋሚው ክፍል መተባበር ቢያንስ ሕውሀት/ኢሕአዲግን ለማስገደድ አስፈላጊ ስለመሆኑ ሸንጎው ያሳስባል፡፡

ተቃዋሚ ከአግላይ ፖለቲካና ከየአውራ ፓርቲ አባዜ ራሱን ማላቀቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንና በሀገራችን ውስጥ በስፋት የቀጠለውን የነጻነት ትግል የወገኖቻችንን በተለይም ወጣቶች ለሰበአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸው መከበር እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠሩ መኖር እንዲያበቃ ለማድረግ ቆርጠው እየታገሉ መሆናቸውና ውድ ህይወታቸውንም ጭምር እየገበሩ እንደሆነ ግልጽ ነው፣ ይህንን መስዋእትነት ለውጤት ለማብቃት በጋራ እንነሳ፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ታላቅነት የዚህች ታሪካዊ ሀገርና ሕዝቧ ታላቅነት እንዲሁም ብሩህ ቀን ከፊት ለፊታችን መሆኑን አበክረው ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር አቻሜየለህ ከሀገራችን የፖለቲካ ትግል ጎንም በሙያቸው ደግሞ ሰለሀገራችን ባህል ወግና ልምድ ታሪካዊ እሰቶችን
 
ለማስተዋወቅና ለታሪክ መዝግቦ ለማቆየት ያደረጉትን ዛሬም በማድረግ ላይ የሚገኙትን እንደዚሁ በመረጃ በተደገፈ መልክ አቀናባብረው ለጠቅላላው ሕዝባዊ ሰብሰባ ተካፋዮች በሚገባ አስረድተውል።

በዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይም በእንግድነት ተጋብዘው ከነበሩት መሀከል እንደዚሁ ከወልቃይት ጠገዴ የአማራ ክልል አከባቢ የልሳነ ጉፉአን ድርጅትን በመወከል አቶ ገብሩ ማማዬ በሰብሰባው ላይ በመሳተፍ የወያኔን መንግስት  በወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን የጅምላ ጭፍጨፋን የዘር ማጥፋት ወንጀልንና ከዚሁም ጋር የወልቃይት ጠገዴን እውነተኛ ማንነትን በተመለከተ ያለውን በተጨባጭ ከታሪካዊ ማስረጃ ጋር በማነጻጸር ለተሰብሳቢዎቹ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከስብሰባው ታዳሚዎች መሀከልም ብዙዎቹ ሰለ ሀገራችን  የፖለቲካ ትግልና በተለይም ዛሬ በየቅጣጫው ተቀጣጥሎ ያለውን ሕዝባዊ ዓመጽን አስመልከቶ የሸንጎውን ሚናና እይታ በምን መልክና ደረጃስ ላይ እንዳለ ለማወቅ ለተጠየቁት ብዙ ጥያቄዎች ፕሮፌሰር አቻሜየለህ ደበላ የሸንጎውን ሚናና እይታ በተለያየ መልኩ በመዘርዘር በተለይም ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የሁላችንም የኢትዮጵያዊያንን መኖርያና መከበርያችን የሆነችውን ኢትዮጵያን በመገንባቱ ረገድ ከእያንዳዳችን የሚጠበቅብንን ዜግነታዊ ድርሻና ሸንጎም እንድ አንድ የጋራ ሕዝባዊ ደርጅት በሀገራችን በፖለቲካው ሕይወት ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ቦታና ሊጫወት የሚችለውንም ሚና በመተንተን ከቤቱ ለተጠየቁት ጥይቄዎች አጥጋቢ መልስ ስጥተዋል።

በመጨረሻም ፕሮፌሰር ኣአቻሜየለህ ደበላ በሀገራችን በየዘርፉ የተከሰተውን ሕዝባዊ ዓመጽና እንቢተኝነት ወደ ተግባር በማድረስ ተደራጅተው በሚገኙትና ሕዝባዊ ድርጅቶችም ሆነ ፖለቲካ ድርጅቶች ሁላችንም እንደዜጋ የበኩላችንን ዜግነታዊ ድርሻ እንድንወጣ በማሳሰብና ከራሳቸውም ልምድና ተመክሮ በመነሳት ለመላው ስብሳባ ተካፋዮች ምክራቸውን በመለገስ ስብሰባው በታቀደው መሰረት በሰላማዊ መንገድ ተጠናቆአል።


ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር

ሐምሌ 09.07.2016
ፍራንክፈርት/ ጀርመን