የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ [ሸንጎ] ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ

mu13

ABOUT SHENGO

                    

አመሰራረት:-

ከሃያ ሁለት ወራት ዝግጅት በኋላ፣ ከግንቦት 10 ቀን እስከ ግንቦት 13 ቀን 2004 ዓ.ም. (ሜይ 2012) ድረስ በካናዳ ዋና ከተማ በኦታዋ የተካሄደው ሁሉን አቀፍ የአንድነት ግንባር ምሥረታ ጉባኤ፣የልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ሲቪክ ማህበራትና ግለሰቦች ተሳትፈውበት በደረሱበት ስምምነት መሰረት “የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ” መመስረቱ
የሚታወስ ነው። የሸንጎው አመራር ምክር ቤት ሥራውን በመጀመር የመጀመሪያውን መደበኛ ስብሰባ በግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም.(28-05-2012) አካሂዷል። በዚህ ስብሰባው የተለያዩ የሥራ ዘርፎችን የዘረጋ ሲሆን በእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ ውስጥ ገብተው የሚያገለግሉትን አባላት መድቧል። የስራ መመሪያዎችንም ሰጥቷል። በሀገራችን ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንደገና ከዳሰሰ በኋላም አንዳንድ ውሳኔዎችን ወስኗል።


በአሁኑ ወቅት በአገራችንና በሕዝባችን ላይ ለደረሰው ውድቀትና ጉዳት ተጠያቂው በሥልጣን ላይ ያለው እብሪተኛና አሸባሪው የሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ መሆኑን ሸንጎው በጥብቅ ይገነዘባል። ይህ ቡድንም ከሥልጣን ተወግዶና አምባገነናዊ ስርዓቱ ተገርስሶ በምትኩ የዜጎች ሁለንትናዊ መብቶች የሚከበርባት፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነባት፣ እውነተኛ
ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እውን የሚሆንባትን ኢትዮጵያን ለማምጣት በጋራ ቆመው ከመታገል የተለየ አማራጭ እንደለለ አሁንም በድጋሜ ያሰምራል። ትግሉ እረጅምና አዳጋች እንደሚሆን ሸንጎው አይዘነጋም።ሆኖም ግን የማታ ማታ ድሉ
የሕዝቡ እንደሚሆን ቅንጣት ያክል ጥርጣሬ አያድርበትም። ለዚያ ድል እውን መሆን ግን መሣሪያው አንድነት ነውና ሁሉም በየፊናውና በተናጠል የሚያደርገውን ትግል በአንድ አቅጣጫ አቀናጅቶ በጋራ አመራር ሥር ቢያካሂደው የሚደርሰውን የሰው ህይወት፣ የንብረትና የጊዜ መጥፋት ከማዳን አልፎ ለድሉ ዋስትና ይሰጣል ብሎ ሽንጎው ያምናል።
ስለሆነም እስከአሁን ድረስ በሸንጎው ውስጥ ያልተካተቱት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራትና ግለሰቦች ጭምር እንዲካተቱ እንዳለፈው ጊዜ አሁንም ጥሪውን ያቀርባል። አሁንም ኑ! በአንድነት እንሰለፍ፤ በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን ግፍና ሰቆቃ፣ የአገራችንን የመበታተን አደጋ በህብረት ተከላክለን እናስወግድ ይላል። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር”
እያለም የህብረትን ጥቅምና ሃይል ያወድሳል። በተጨማሪም ሸንጎው በስልጣን ላይ ያለው ቡድን፣-
• በነፃ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ድርጅት አባላት ላይ የሚያደርገውን ማሳደድና በአሸባሪነት ስም እየወነጀለ በእስር ቤት ውስጥ እያጎረ ማንገላታቱን ያወግዛል ።


• በሕዝቦች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠርና ወደከፍተኛ ቀውስ እንዲገባ የሚደረገውን
ተንኮልና የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በጥብቅ ያወግዛል።
• በእስልምናና በክርስቲያን ሃይማኖት ተቋማትን የማፈራረስና በምዕመናኑ ላይ
የሚያደርገውን የመከፋፈል ሴራና ተንኮል ያወግዛል፣ያጋልጣልም።የሁለቱም እምነት
ተከታዮች የአምባገነኑን ቡድን ተንኮል ተረድተውና ጠላታቸው በስልጣን ላይ ያለው
ቡድን መሆኑን አውቀው፣ በአንድ ላይ በመቆም በፍጹም ኢትዮጵያዊነት በጋራ
እንዲታገሉት ጥሪ ያቀርባል።
• በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በደቡብና በምሥራቁ ያገሪቱ ክፍል የገዢው ቡድን ያሰፈነው
ሥርዓት እያካሄደ ያለውን ጭፍጨፋና ሕዝብን የማሸበር ተግባር በጥብቅ
ያወግዛል።
• ገበሬውን ከሚያርሰው መሬት በማፈናቀል፣ የሀገሪቱን ለም የእርሻ መሬቶች ለሥርዓቱ ደጋፊዎችና ተባባሪዎች

እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ባለጸጎች መሸጥና የአገሪቱም ዳር ድንበር እየተቆረሰ ለጎረቤት አገር አሳልፎ መሰጠቱን በጥብቅ
ይቃወማል። የሀገሪቱ ሕዝብም ከተጎዱት ወገኖቹ ጎን እንዲቆም እንዲሁም ለሃገሩ ዳር ድንበርም አባቶቹና እናቶቹ እንዳደረጉት ሁሉ በጋራ ዘብ እንዲቆም ጥሪ ያስተላልፋል።
ሸንጎው በኢትዮጵያዊነታቸው፣ በኢትዮጵያ አንድነት፣ በሕዝቡ ሰላማዊ ኑሮ፣ እድገትና እኩልነት፣ በዲሞክራሲ ሥርዓት መስፈን ፣ በሕግ የበላይነት፣ የሚያምኑ ሁሉ ጎሳ፣ እምነት፣ ክልል፣ ቋንቋ፣ እድሜና ፆታ ሳይለያቸው በፍጹም ኢትዮጵያዊነት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሸንጎው በተለመው የትግል አቅጣጫና ሰልፍ ውስጥ እንዲገቡ ጥሪውን ያስተላልፋል።
መጥራት ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚ ሃይሎች በሚጠሩት ስብሰባና በሚከፍቱት የውይይት መድረክ ላይ ለመገኘት ምን ጊዜም ዝግጁ ነው።በመቀራረብና አብሮ በመሥራት ያምናል።ስለሆነም በቅርቡ በዋሽንግተን ከተማ ውስጥ በተካሄደው የወጣቶች ንቅናቄ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፍ የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ተወካዮቹ እንዲገኙ አድርጓል። ወደፊትም በዳላስ ከተማ በሚደረገው “የብሔራዊ የሽግግር ካውንስሉ ስብሰባ” ላይ እንዲገኝ ስለተጋበዘ ግብዣውን ተቀብሎ ለመገኘት ወስኗል።
የብዙሃን የመገናኛና የዜና አውታሮችም የጋራ ትግሉ በሚጠናከርበት አቅጣጫ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉና እንዲተባበሩ ይጠይቃል።


“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር”
ኢትዮጵያ በነጻነትና በአንድነት ለዘለዓለም ትኑር!!
ዘረኛውና አገር በታታኙ ሥርዓት በሕዝባዊ ሥርዓት ይተካ!!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ