የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ [ሸንጎ] ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ

home

የሁሉም የህሊና እስረኞች መፈታትና የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር፣ ሙሉ ምላሽ የሚሻ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ነው።

ሐምሌ 2፣ 2007 ( ጁላይ 9፣ 2015)

ከዓመት በላይ ያለአግባብ አስሯቸው ካቆየ በሁዋላ የወያኔ/ ኢህአዴግ መንግስት ጦማሪያን ኤዶም ካሳዬን ዘላላም ክብረትን፣ ማህሌት ፋንታሁንን እንዲሁም ጋዜጠኛ ተስፋለም  ወልደየስና  አስማማው ሀይለጊዮርጊስን ትላንት ሀምሌ 1 ፣ 2007 ( ጁላይ 8፣ 2015) በዛሬው ዕለት ደግሞ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙን ካመታት እስር በሁዋላ ድንገት እንደፈታቸው ታውቋል።

ግለሰቦቹ  ቀድሞም  የታሰሩት  የጋዜጠኛ  ሙያቸውን   ሲወጡና   ሀሳብን   በነጻ   የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ በማድረጋቸው እንጂ ሌላ ወንጀል ፈጽመው  አልነበረም።  በመሆኑም  እንኳንስ ለረጅመ ጊዜ ለአንድ ሰአትም ቢሆን መታሰር አይገባቸውም ነበር። የስርአቱ የጸጥታ ሀይሎችና ካድሬዎች በዚሁ የጥፋት ጎዳና በመቀጠል ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ በሰላዋሚ መንገድ ለመብታቸው የቆሙ እጅግ ብዙ  የፖለቲካ  ተቃዋሚ  ድርጅቶች  (በተለይም  የመድረክ  የሰማያዊ  ፓርቲና  የመኢአድን)  አባላትና ደጋፊዎች አስረዋል፤  ደብድበዋል፤ ገድለዋል።  ይህን ቀጣይ የመብት ረገጣ ሽንጎው በጥብቅ  ያወግዛል።

ከላይ የተጠቀሱት ስድስት ግለሰቦች ከእስር መፈታት የሚደገፍ ሲሆን የወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት በተመሳሳይ ሁኔታ በየእስር ቤቱ በሰበብ ባስባቡ አፍኖ እያሰቃያቸው የሚገኙትን እነ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ ፣ ውብሸት ታየና ሌሎችንም ጋዜጠኞች እንዲሁም አንዱአለም አራጌ፣ ሀብታሙ አያሌው፤ አቡበከር አህመድ፤ አብርሀም ደስታን፤  የሽዋስ  አሰፋ፣  ዳንኤል  ሽበሽ፤  ኦልባና  ለሊሳና በሽዎች የሚቆጠሩ ሌሎችንም የፖሊተካ እስረኞች ባስቸኳይ እንዲፈቱ፤ ከየቦታው ተወስደው ከዘመድ አዝማድና ከህዝብ እንዲሰወሩ የተደረጉ ዜጎች የት እንደደረሱና በምን ሁኔታ እንደሚገኙ እንዲያሳውቅ ሸንጎው አጥብቆ ይጠይቃለ። ባጠቃላይም ኢትዮጵያ ዛሬ ከገባችበት ችግር እንድትወጣ ይቻላት ዘንድም ገዥው ቡድን በዜጎች ላይ የሚያካሄደውን የመብት ረገጣ ባስቸኳይ እንዲያቆምና ያሉትን ችግሮች ለመፍታትም ሆነ የወደፊቱን ዕክል ለመቋቋም ብሄራዊ መግባባትና እርቅን መሠረት በማድረግ እንዲነሳ አሁንም  እናሳስባለን።

ድል ለኢትየጵያ ህዝብ

To read in pdf

 

Hits: 2803

የ2007ቱ ሀገራዊ ምርጫ አካሄዱና አፈጻጸሙም ነጻና ፍትሀዊ ስላልሆነ ውጤቱን ሸንጎ አይቀበለውም።

ግንቦት 17፣ 2007 (ሜይ 25፣ 2015)

ገና ከጅምሩ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን መሪዎችንና አባላቶቻቸውን በማሰር፣ በማሳደድና በማዋከብ፤  ነጻ የሃሳብ ልውውጥ እንዳይኖርና  አማራጭ ሃሳቦች ለህዝብ እንዳይደርሱ ነጻ የመገናኛ  ብዙሃን ጋዜጠኞችንና ጦማራውያንን በግፍ ወደ እስር ቤት በመወርወርና  የሚወዷትን ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ በማድረግ፤ ከአገዛዙ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በጭቆና መሣርያነት የሚያገለግለውን የምርጫ ቦርድ በመጠቀም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማፈራረስ የተጀመረው ምርጫ ተብየ በትናንቱ እለት ተካሂዷል።

በዚህ ምርጫ ተብየ፣ የተስተዋለው ድባብ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን መፈናፈኛ በሚነሳ ሁኔታ እግር ከወርች አስሮ በተለያየ አሻጥር ቀፍድዶ እንዳይንቀሳቀሱ የሆነበት አካሄድ በግልጽ ሲታይ በአኳያው ደግሞ የገዠው ፓርቲ የሀገሪቱን ሀብትና ንብረት ገደብ በለለው ሁኔታ ለራሱ ጠቀሜታ እንደፈለገ ሲያውላቸው ተስተውሏል።.......ሙሉውን ለማንበብ ይህን ይጫኑ

Hits: 2304

ሚስ ዌንዲ ሸርማን በቅርቡ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ የስጡት አስተያየት የተሳሳተና ጎጂ ነው

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ከብዙ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ እንዲሁም ነጻ ከሆኑት የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ ከፍሪደምሃውስ፣ ከሂውማንራይትስዋች፣ ከአምነስቲኢንተርናሽናል፣ ከኢንተርናሽናል ሪቨርስና ከሌሎቹ ጋር በማበር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የፖለቲካ ቢሮ ም/ሃላፊ የሆኑት ዊንዲ ሸርማን በቅርቡ ባደረጉት የአዲስ አበባ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ወቅት በ16-04-2015 የሰጡት አስተያየት እውነትን የማያንቀባርቅ በመሆኑ ከማዘናችንም በላይ የአሜሪካንንም ሆነ የኢትዮጵያን መሰረታዊ ጥቅም ሊያሰከብር የሚችል እንዳልሆነ መግለጽ ይወዳል፡፡

ካሁን በፊት የአሜሪካ መንግስት በተደጋጋሚ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ እስራት፣ ማሳደድ፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ አፈና፣ በግዳጅ መሰወር፣ የአካል ጉዳትና ስቃይ ማድረስና ሕዝቡን ለባርነት አሳልፎ መስጠት አሁን በስልጣን ላይ ባለው  መንግስት የሚፈጸም እለታዊ ተግባር እንደሆነ አረጋግጧል። ይህንኑም ግፍና በደል ያሜሪካን ባለስልጣናት ራሳቸው በአካል በማየትመንግስት ከዚህ አይነቱ ተግባር እንዲታቀብና ጋዜጠኞችና ጦማርያንም እንዲፈቱ ጠይቀዋል ጨቋኝ ህግጋትም እንዲለወጡ አሳሰበውነበር።

ይህአይነቱ  ግፍና ወንጀል የሚፈጽም መንግስት ባለበትአገር፣ ሚስ ሸርማን “ኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው ዲሞክራሲ በየቀኑም እየጎለበተ ነው፣ የሚመጣውም አገር አቀፍ ምርጫ ሁሉን አቀፍ በሚያደርግ መንገድ እየተዘጋጀ ነው” ብለው ማለታቸው ከብዙሃኑ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካ መንግስት በጽሁፍ ካሰፈራቸው መረጃወችና መግለጫወች ጋር የሚቃረን ነው ብለን እናምናለን።....... ሙሉውን ለማንበብ ይህን ይጫኑ

Hits: 2123

'አይሰስ' በማለት ራሱን የሚጠራው ቡድን በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ሸንጎ በጥብቅ ያወግዛል!

 

፲፪ ፣ ፳፻፯    April 20, 2015

አይሰስ በማለት ራሱን የሚጠራው ቡድን በሊቢያ ውስጥ በሁለት የተለያዩ ክፍለሀገሮች በያዛቸው ኢትዮጵያውያን ላይ ያለርህራሄና አረመኔያዊ በሆነ መልክ ያካሄደውን ግድያ አለም እንዲያይለት ለማድረግ ያሰራጨውን ቪድዮ የተመለከትነው በከፍተኛ ሃዘንና ቁጭት ነው። ለተጠቁትም ቤተሰቦች ጥናቱን ያገኙ ዘንድ እየተመኘን ይህን ሰብዓዊነት የጎደለውን ተግባር  ሸንጎው በጥብቅ ያወግዛል።

ይህ ቡድን እነዚህን ኢትዮጵያውያን አንገታቸውን  በመቅላትናበጥይት በመደብደብ ያካሄደው ግድያ በንጹሃንና ምንም ወንጀል ባልሰሩ ነገር ግን ክርስትያንና ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው ብቻ መሆኑ የቡድኑ ተግባር መሰረታዊ የእስልምና እምነትን የሚጻረር ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ  የሰው ልጅ ርህራሄ የጎደለው እንደሆነም ያሳያል። ስለሆነም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ የየትኛውም እምነት ተከታይ ይሁን፣ የፖለቲካ አመለካከት አራማጅ፣ ይህንን ተግባር በአንድ ድምጽ ሊያወግዘው ይገባል። በማንኛውን ኢትዮጵያዊ ላይ የሚፈጸም የግፍ ተግባር በሁላችንም ላይ እንደተፈጸመ የሚቆጠር ነውና በሊቢያ ውስጥ  በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን ግፍ በጋራ እንድናወግዝ ጥሪያችንን እናቀርባለን።  .......... ሙሉውን ለማንበብ ይህን ይጫኑ

Hits: 2456

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ አመራር ምክር ቤት የተሳካ ጉባኤ አካሄደ

በቅርቡ የሽንጎው ከፍተኛ አመራር አካል የሆነው ምክር ቤት ባካሄደው የሁለት ቀን ስብሰባ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ሁኔታ በሰፊው መርምሮ ለቀጣዩም ትግል ምን መደረግ እንዳለበት መመሪያ በመሰጠት ተጠናቋል።

በተጨማሪም የሽንጎው የተለያዩ የስራ ክፍሎች የስራ አፈጻጸምን በተመለከተ የቀረቡለትን ሪፖርቶች መርምሮ ትግሉ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን ተጨማሪ መመሪያ በመስጠት ተጠናቋል። በተለይም ደግሞ ሽንጎው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያካሂደው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ የተገኙትን መልካም ግንኙነተቶችን እና አበረታች ውጤቶች ከመረመረ በኋላ በዚህ መስክ የሚካሄደው እንቅስቃሴ እጅግ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መመሪያ ሰጥቷል፡

የሸንጎው ምክር ቤት የኢትዮጵያን አጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታ የገመገመ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ውስጥ እጅግ ተጠናከሮ የቀጠለውን ሁለንተናዊ የመብት ረገጣ ፣ በተለይም ደግሞ ባሁኑ ሰአት ዜጎች መሰረታዊ የሆነውን መሪዎቻቸውን በድምጻቸው በነጻነት የመመምረጥ መብታቸውን በትክክል እንዳይገልጹ ገዥው ሕወሀት/ኢህአዴግ እና እንደልቡ የሚያዛቸው የምርጫ የጸጥታና የፍትህ ተቋማት በህዝባችን ላይ በቀጣይነት እያሳዩት ያለውን እጅግ አሳዛኛ ግፍ ባፅጽንኦና በታላቅ ሀዘን ተገንዛቧል።

በዚህ እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ፣ የፖለቲካ መድረኩን ለገዥው ቡድን ባለመተው የህዝባችንን መብት ለማስከበር እጅግ ብዙ መስዋእትነት ለከፈሉ እና በመክፈል ላይ ለሚገኙ ታጋዮች ሁሉ ያለውን አድናቆት አክብሮትና የትግል አንድነት ምክር ቤቱ በድጋሜ አረጋግጧል።

ገዥው ቡድን ህወሓት/ኢህአዴግ የህዝባችንን መብት በሁሉም መልኩ መርገጡን በቀጠለ ቁጥር ህዝባችን ደግሞ በስርዓቱ ላይ ያለው ብሶት፣ ቅሬታና ጥላቻ እጅግ እየሰፋ መምጣቱን፣ የሚደርስበት ግፍ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ እንደሆነም ብዙ መረጃዎችን ምክር ቤቱ ተመልክቷል። ዛሬ ህዝባችን ከዚህ ስርዓት መልካም ነገርን መጠበቅ ትቷል። በራሱ አነሳሽነት ስርአቱ እንዲወገድለት አምርሮ ይፈልጋል። አልገዛም ማለትን በየቦታው እያሳየ ነው። ለመብቱ መቆሙን በግልጽ ማሳየቱን ቀጥሏል። የፍርሀት ድባብን አፈራርሶ በመጣል ላይ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪም በገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ የርስበርስ አለመተማመንና ውጥረትም እየሰፋ መምጣቱን የሽንጎው ከፍተኛ አመራር ምክር ቤት በሰፊው ቃኝቷል።

እነዚህን ሁሉ ባንድ ላይ ስንመለከትም ሀገሪቱ ውስጥ ህዝባዊ የለውጥ አመጽ ሊነሳ የሚችልበት ሁኔታ እጅግ በፍጥነት እየተቃረበ መሆኑን ሽንጎው ተገንዝቧል።
ገዥው ቡድን ከላይ ሲታይ ሁኔታዎችን የተቆጣጠረና የተረጋጋ ይምሰል እንጂ ከሁሉም ህዝብ፣ ከሁሉም ፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማህበራት የሀይማኖት ተቋሞች ጋር የገባበት ቅራኔ የራሱን ጥላ ሳይቀር ማንንም እንዳያምን ስላደረገው እነሆ ሌትም ቀንም በመደናበር፣ ከአንዱ ስህተት ወደሌላው እየተላተመ ወደ መጨረሻው መቃብሩ እንደተቃረበ እንረዳለን።

ሀላፊነት የጎደለው ይህ ጠባብ ቡድን፣ ከራሱ ስልጣን እና አልጠግብ ባይ ዝርፊያ ባሻገር ለማገናዘብ ባለመቻሉም ሀገሪቱን ራሷን ወደ አደጋ አፋፍ አድርሷታል።

ይህን ሀገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ የሚከታተሉ የሀገሪቱ ጠላቶችም የህዝባችንን የለውጥ እንቅስቃሴ ለአደጋና ለራሳቸው ቀጣይ አጥፊ አጀንዳ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ሸንጎ ተገንዝቧል።

ሀገራችንና ህዝባችን ከታሰሩበት የግፍ ሰንሰለት ነጻ ለማውጣትና በምትኩም አንድነቷ በተጠበቀ ኢትዮጳያ ስር ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲአዊ ስርአትን ለመገንባት የሚደረገው ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሽንጎው ምክር ቤት መመሪያ የሰጠ ሲሆን፣ ይህን ትግል ወደግብ ለማድረስም ሆነ ከላይ የጠቀስናቸውን አሳሳቢ ሁኔታዎች ለማስወገድ ያንድነት ሀይሎች ከምን ጊዜውም በላይ በመተባበር በንቃት እንዲንቀሳቀሱ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
 ሀገራችን ከምትገኝበት አስከፊ ሁኔታ ሁሉም አሽናፊና ተጠቃሚ ወደሆነበት ስርአት ለመሽጋገር ብሄራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ አማራጭ የሌለው እንደሆነ ምክርቤቱ አጽንኦ ሰጥቷል።

የሸንጎው ያመራር ምክር ቤት ዛሬ በሚካሄደው ትግል ውስጥ ያማራጭ  መገናኛ ብዙሃንን አስፈልጊነት በሰፊው ከተወያየ በኋላ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፍ ያጭር ሞገድ ሬዲዮ ፕሮግራም ባስቸኳይ እንደሚያስፈልግና፣ ይህን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ እና ጊዜያቸውን በማበርከት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

Hits: 1742