የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ [ሸንጎ] ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ

home

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ (ሽንጎ) የአመራር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ። የወቅቱን ሁኔታ ገምግሞ፣ የጋራ ትግሉን ለማጠናከር ተጨማሪ መመሪያ ሰጠ።

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ (ሽንጎ) የአመራር ምክር ቤት ቅዳሜ ጥር 28፣ 20008 (Feburuary 6, 2016) መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል። በዚህ ጉባኤው ምክርቤቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ሁኔታ፣ በህዝባችን ትግል አኳያ የሚታዩትን ተስፋ ሰጭ ገጽታዎችና  አሳሳቢ ክስተቶችን በሰፊው ገምግሟል።  የሸንጎ የተለያዩ የስራክፍሎች የሚያካሂዱትን ተግባር በተመለከተ የቀረቡትን የስራ ዘገባዎች መርምሯል፡፡ በመቀጠልም በህዝበችን ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ግፍ ሊያከትም እንዲችልም መካሄድበሚገባው ትግል ላይ አስፈላጊውን የተግባር መመሪያዎች ሰጥቷል፤ የትግል ጥሪም አስተላልፏል።

የ25 ዓመቱ የህወሀት/ኢህአዴግ የአምባገነን የግፍ ስርአት ኢትዮጵያን አደጋ ላይ ጥሏል። ኢትዮጵያውያንን አስመርሯል። በሁሉም የሀገራችን ክፍል የሚገኘው ኢትዮጵያዊህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እውን የሚሆንበትን ጊዜ ናፍቋል።  መናፈቅ ብቻም ሳይሆን፣ አንድነቷ በተጠበቀ ኢትዮጵያ ስር መብቱን ለማሰከበር፣ የህግየበላይነትን እውን ለማድረግ፣ ከፋፋይ ስርአትን ለማስወገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየቦታው ተቃውሞውን በተለያየ መልክ በመግለጥ ላይ ይገኛል።ህዝባችን በተለያየየሀገሪቱ ክፍል መብቱን ለማስከበር ከፍተኛ መስዋእትነትን በመክፈል ላይ ነው። ስርአቱ በመፍረክረክ ላይ ይገኛል። ክንዱ ዝሏል። አደንቋሪ ፕሮፓጋንዳውንየሚያዳምጠውጆሮ አጥቷል። በሀገራችን ውስጥ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው ሀገራችን  የለውጥ ዋዜማ ላይ መሆኗን ነው።

በዚህ አኳያ በአሁኑ ሰአት በመላ ሀገራችን በተለይም ደግሞ ኦሮሚያ፤ አማራና ጋምቤላ ተብለው በሚታወቁት ክልሎች  እየተካሄደ ያለውን  የመሰረታዊ  መብቶችመገፈፍን፤የመሬት ቅርምትንና ዘረፋን፣ ዳር ድንበርን ማስደፈርን፣  አግላይ የሆነን ፖለቲካና ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ተግባር የመቃወም ትግልና ህዝባዊ እምብተኛነት ሸንጎው ከዚህ በፊት ደጋግሞ  እንዳደረገው ሁሉ  አሁንም በጽኑ ይደግፋል።  መራራውን ጭቆናና ግፍ ባልተቋረጠ መልክ በህዝብ ላይ የጫነውን አገዛዝ በማስወገድ  ዴሞክራሲያዊ ስርዓትንና  በእኩልነት ላይ የተመሰረተን አንድነት ለመመስረት ትግል ከሚያደርጉ ሁሉ ጋር  የትግል  አጋርነቱን ይገልጻል።  

ስርአቱ ለዚህ የህዝብ ትግል ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ እንደተለመደው በማን አለብኝነት ለማፈን የሚወስደውን የሀይል እርምጃ፣ እስራት፣ ድብደባና ግድያ ምክር ቤቱ ያወግዛል።  በደል ለደረሰባቸው ሁሉም የሀዘናቸው ተካፋይነቱን ይገልጣል።  ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞም የታሰሩት ሁሉ ባስቸኳይእንዲለቀቁ፣  ንብረታቸው ለጠፋው እንዲሁም በስርአቱ የጸጥታ ሀይሎች ለተገደሉ አስፈላጊው ህጋዊ ካሳ ለቤተሰቦቻቸው እንዲከፈልና ገዳዮቹም ሆኑ ትእዛዝ ሰጭዎችለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ  ትግሉን እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ይህን የህዝብ ትግል ለጠባብና ከፋፋይ አላማ ሊያውሉት የሚጥሩትን አንዳንድ የውስጥም የውጭም ሀይሎች እንዲሁም የስርአቱን ደባ ሁሉምኢትዮጵያዊ በጥንቃቄ ነቅቶ እንዲከታተልና የከፋፋዮች ሰለባ እንዳይሆንም ነቅቶ እንዲጠብቅ አሳስቧል።

የህዝባችንን  የትግል መነሳሳት ወደተፈለገው የስርአት ለውጥ እንዲያመራ የተቃዋሚው ወገን ታላቅ ሀላፊነት እንዳለበትና  በተናጠል የሚደረግ ትግል ለስርአቱ  እድሜመራዘም የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ ይህን ሁኔታ ለመቀየር የሚያሰችል አስተማማኝና ቀጣይ ትግል ለማካሄድ ከሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር በጋራለመስራት በሽንጎው በኩል የሚደረገውን ጥረት ከመረመረ በኋላ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮና ቅድሚያ ተሰጥቶት አንዲቀጥል፣ ሌሎች የአንድነት ሀይሎችም የጋራ ትግሉንእውን ማድረግ አጣዳፊነት ተረድተው ጠንካራ የተቃዋሚ ህብረት በመመስረቱ ተግባር ላይ በጋራ መረባረብ ይገባቸዋል ሲል ምክር ቤቱ ለሁሉም የአንድነት ሀይሎችየትብብር ጥሪውን በድጋሜ አስተላልፏል።

የህወሀት/ ኢህአዴግ አምባገነን ስርአት ዕለታዊ ተግባር በሀገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ እያደረገ እንደሆነ አለም አቀፍ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ  ይህን አደጋ ለማስወገድም የኢትዮጵያ ህዝብ  ለመሰረታዊ መብቱ መከበርና ፣ ለህግ የበላይነት  የሚያካሂደውን ትግል  እንዲያግዝ  ከምን ጊዜውም የላቀ ዲፕሎማሲያዊ  ትግልእንዲካሄድ ምክር ቤቱ ተጨማሪ መመሪያ ሰጥቷል።

በመጨረሻም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመሰረታዊ ጥያቄዎቹ መልስ ማግኘት ማለትም ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር፣ ራሱ የመረጠውና የሚቆጣጠረውመንግስት ለመመስረት፣ ለህግ የበላይነት መከበር፣ የከፋፋይ ስርአት እንዲያከትም የፖለቲካ ስርአቱ ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ተሳታፊ የመሆን  መብቱ እንዲከበር፣በነጻነትና ያለፍርሃች መኖር እንዲችል የኢኮኖሚ ተስፋ፣ የማሀበራዊ  ፍትህ ፣ እውን  እንዲሆን ሁሉም  ዜጋ ማንነቱ ተከበብሮ በቋንቋው የመጠቀም፣ ባህሉን  የማዳበር፣መብቱ ተጠብቆ መኖር...ወዘተ እንዲችል  ለሚደረገው  ትግል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የትግል አጋርነቱን እንዲገልጥ የአንዱ ኢትዮጵያዊ መጠቃት የሌላው መጠቃት እንደሆነበመገንዘብ እጅ ለእጅ  በመያያዝ በተባበረ ትግል የጭቆናውን ስርአት ለማስወገድና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት  የሚያሰተናግድ ህገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአትለመመስረት በጋራና በመተጋገዝ  እንዲታገል የሸንጎው  የአመራር ምክር ቤት ጥሪ አድርጓል።

ድል  ለኢትዮጵያ  ህዝብ

Hits: 1630

የህዝቡ መነሳሳት ሁሉን አሳታፊ የሆነን የስርዓት ለውጥ ለማምጣት እንዲችል ምን ይደረግ?

 

ሕዝብ መብቱን ሲነፈግ፣ያገሩ ክብርና አንድነት ሲደፈር፣በሰላም ሠርቶ ማደር ሲሳነው፣በኑሮ ውድነትና በሥራ አጥነት ሲወጠር፣ጭራሽ የመኖር ተስፋው ሲጨልም ከትዕግስትና ከመንፈሳዊው የትግል ዘዴ ከጸሎት ወጥቶ በአደባባይ በሚገለጽ ተቃውሞ ውስጥ ለመሳተፍ ወይም ነፍጥ አንስቶ ለመፋለም ይገደዳል።በዚህም የትግል ሜዳ ውስጥ ሲገባ  አምባገነን መንግስት ጉንጉን አበባ ይዞ እጁን ዘርግቶ እንደማይቀበለው ያውቀዋል።ከመንግሥት ሊሰነዘር የሚችለውን የበቀል አመጽ አይዘነጋውም። መሞት፣መቁሰል፣መደብደብ፣መታሰርና መንገላታት እንደሚኖር ገና ከጥዋቱ  ቢረዳም ድምጹን አጥፍቶ፣አንገቱን ደፍቶ ከመኖር ይልቅ የመጣውን ለመቀበል ቆርጦ ያልሞት ባይ ተጋዳይ እርምጃ  ይወስዳል።

ሕዝብ ለሚወስደውና ለሚከተለው የትግል አቅጣጫ መሰረቱ መዋናነት የህዝቡን ጥያቄ ለመስማት የማይሻ፣በራሱ እብሪት የሚመራ አምባገነን መንግሥት በስልጣን ላይ መኖሩ ነው።ሕዝቡ በተደጋጋሚ ለሚያሰማው እሮሮ መልስ ካላገኘ ደፍሮ አደባባይ መውጣቱ የማይቀር መሆኑ በተደጋጋሚ በአገራችንና በሌሎች አገሮች የታዬ ሂደት ነው።የሂደቱ መደምደሚያ የሚሆነው ይዋል ይደር እንጂ የሕዝቡን ጥያቄ የማይቀበሉ መንግሥታት ተወግደው ስልጣኑ በሌሎች እጅ መውደቅ ይሆናል።

በሕዝብ ትግል ሳቢያ ሊመጣ የሚችለው ለውጥና የሥልጣን እርክክቦሽ በተለያየ፣ማለትም በጠቃሚና በጎጂ አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል፤

አንደኛ ሕዝብ በቅጡ እንዲደራጅና ሁሉም በትግሉ ተሳታፊና የውጤቱ የጋራ ባለቤት እንዲሆን፣ከጎጠኝነት የራቀ በልበ ሰፊነት በቀልን አሶግዶ በመቻቻል፣አገር አድኖ ሕዝብ ለማዳን ጥረት የሚያደርግ  ከሁሉም የተውጣጣ ትግሉን የሚመራ አካል ከተፈጠረ የሚመጣው ለውጥ ተስፋ ሰጭና ለሁሉም የሚጠቅም ይሆናል።

በሌላው አቅጣጫ ደግሞ በሕዝቡ ትግል ጀርባ የሕዝቡን መብት እና ጥያቄ እያነሱ ግን ሁሉም ሕዝብ የሚሳተፍበትን መድረክ እያጠበቡ በተወሰኑ ሃይሎች ብቻ የሚመራ፣ሌሎችን ያገለለና ያራቀ፣ በጠባብ ቡድናዊ ስሜትና የተወሰኑ ክፍሎቸ ጥቅም ላይ ያተኮረ አመራር በመፍጠር መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ባይቻልም እንደ አጋጣሚ ስልጣን ለመያዝዕድሉና ሁኔታው ቢፈቅድ የሚመጣው ለውጥ የስርዓት ሳይሆን የባለስልጣኖች መቀያየር ይሆንና ሕዝቡን በአዲስ ጉልበተኞች ለቀጣይ ስቃይና ስርዓት የሚዳርግ  ይሆናል።የዚህም ሂደት ውጤት በተደጋጋሚ በተለያዩ አገሮች ሲከሰት የታዘብነውና የምናውቀው ነው የዚህ አይነቱ ለውጥ በአገራችን በኢትዮጵያ እንዲከሰት የሚሻ ቀና ልቦናና ጤነኛ አይምሮ ያለው ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብለን አንገምትም። ይህ ማለት ግን በዛ አይነት አሰራር  ውጤት ለማምጣት የተሰለፉ የሉም ማለት አይደለም፤ አሉ።መኖራቸውም በተደጋጋሚ በሚያደርጉት የአግላይነትና የተንኮል ሴራ የተረጋገጠ ነው።

በአገራችን በሁሉም አቅጣጫ ይብዛም ይነስም ሕዝባዊ ተቃውሞ በተለያየ ደረጃና መልክ ሲገለጽ ቆይቷል።አሁን የዛ የተለያየ የሕዝብ ተቃውሞ እየሰፋና እየጠነከረ መንግሥትን ከሚያሰጋበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል።ግምቱን ወደ ውጤት ለማሻገርር የሚቀረው ነገር ቢኖር ትግሉን አቅጣጫ የሚያሲዝና የሚመራ ሃይል  ከመፍጠሩ ላይ ነው።አሁንም በየፊናው ተከፋፍለው የሚጮሁ ድርጅቶች አልጠፉም እንደውም ቁጥራቸው ጨምሯል።

በአሁኑ እየተጋጋለ በሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት መኖራቸው የማይታወቅና ጠፍተው የነበሩ አንዳንድ ድርጅቶች ሳይቀሩ አንገታቸውን ብቅ ብቅ በማድረግ ውድድር ውስጥ እየገቡበት ነው።፣ ትላንት ከትላንት ወዲያ ኢትዮጵያንና ኢዮጵያዊነትን ሲያወግዙ የተደመጡ ሃይሎች ሳይቀሩ ለሕዝብ አንድነትና ጥቅም የቆምን ነን እያሉ መናገር ከጀመሩበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

ቀድሞም ሆነ አሁን ወደፊትም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ መብት፣የአገር ሰላምና አንድነት ሊጠበቅ የሚችለው ሁሉም ተባብሮ መታገል ሲችል ብቻ እንደሆነ ከታሪካችንና ከውድቀታችን ልንማር ይገባል።በተናጠል ወይም በውጭ ሃይሎች እርዳታና ድጋፍ  በጥቂቶች የሚመጣ ለውጥ ከድጡ ወደ ማጡ እንጂ ወደተሻለ ስርዓት አይወስድም።

 የሁሉም ዜጋ ጥያቄና ፍላጎት በዋናነት ተመሳሳይ ነው፤የአማራው ከኦሮሞው፣ከትግራዩ፣ከአፋሩ፣ከደቡቡ፣ ከጋምቤላው፣ከጉራጌው…ወዘተ የተለየ ፍላጎት የለውም።ሰብአዊ መብቱ፣የዜግነት መብቱ ተከብሮለት በአገሩ ሊያገኝ የሚገባውን ድርሻ አግኝቶ እሱም የድርሻውን አበርክቶ በክብር መኖር ነው የሁሉም ፍላጎት።የየክልሉ አርሶ አደር ጥያቄ የሚያርሰው መሬት ባለቤትነትን፣መፈናቀል እንዲቀርለት በገፍ የሚከፍለው ግብርና የማዳበሪያ ዋጋ እንዲቀነስለት፣ልጆቹን አስተምሮ ለማሳደግና ለቁም ነገር ለማብቃት በሀገሩ ጉዳይ ላይም ሙሉ ተሳታፊ መሆን እንጂ ሌላ ምኞትና ፍላጎት የለውም።የየብሔሩ ወጣትም እንዲሁ ተምሮ የመስራትና በአገሩ ተከብሮ እየኖረ የበኩሉን ለአገሩ ለማበርከት እንጂ ሌላ ምኞት የለውም።ሁሉም ከችግርና ከመከራ ኑሮ ተላቆ መብቱ ተከብሮለት በሰላም መኖርን ይሻል።ትልቅና የበለጸገች ኢትዮጵያ፣ለዜጎቿ የምትመች ኢትዮጵያ፣የእራሷን ጥቅምና ክብር፣ዳርድንበር አሳልፎ የማይሰጥ መንግስት ያላት ኢትዮጵያ እንድትኖረው የማይመኝና የማይፈልግ የለም።

ይህ  የጋራ ሕዝባዊ ፍላጎት ወደ ተግባር ሊተረጎም የሚቻለው ሁሉንም በአንድነት አስተባብሮ ሊመራ የሚችል፣የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ከሕዝብ ጋር አብሮ የሚመክር መንግስት ሲኖር ብቻ ነው።ያ መንግስት ደግሞ በጥቂቶቸ ፍላጎትና ጥረት የሚፈጠር ሳይሆን ሁሉም አውጣጥቶ በጋራ የሚፈጥረው በተለይም እርስበርስ  ማጋጨትን፣ መከፋፈልን “እኛና እነሱ “ የሚል አግላይ መርሆና መርሃግብር ማጠንጠኛው ያላደረገ  የህብረተቡንም አመኔታ ያገኝ ስርአትና መንግስት ሲፈጠር ብቻ ነው።

በተመሳሳይ በጠባብና አግላይ አስተሳሰብ የሚመራ ተለያይቶ የቆመ ቡድን የሚያስተጋባው ጥሪና  የሚመራው ትግል የሚያመጣው ለውጥ ካለውና ሁሉም ከሚጠላውና ከሚታገለው የወያኔ ስርዓት የተሻለ አይሆንም። ስለሆነም የዚህ አይነት የትግል ሂደት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በቅድሚያ አውቆ አደጋው እንዳይከሰት መከላከያ ማበጀት ለጋራ ሕዝባዊ ጥቅምና ደህንነት የሚያስቡ ሁሉ ድርሻና አላፊነት ነው።በዝምታና በቸልታ ከዳር ቆመው የሚታዘቡት ድራማ አይደለም፣ነገ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ማጤኑና መዘጋጀቱ በተግባርም የትግሉ ተሳታፊ በመሆን የወደፊቱን አቅጣጫ ለሁሉም በሚበጅ መንገድ እንዲሆን የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

እውነት ሁሉም የተቃዋሚ ሀይሎች የአምባገነንነትን ማብቃት የሕዝቡን አብሮ መኖር፣የአገራችን ኢትዮጵያን አንድነትና ልዑላዊነት የምንሻ ከሆነ በአንድነት አብረን የጋራ ሃይል የሚፈጠርበትን ዘዴ ባሰቸኳይ መሻት ይጠበቅብናል። ያ ደግሞ  በቀጠሮ የምናስቀምጠው ወይም ለተወሰኑ ቡድኖች በጎ ፈቃድ የምንተወው ሳይሆን ለዛሬው ያገራችን ሁኔታ  ሁላችንም የምንሰጠው አስቸኳይና ትክክለኛ መልስ ይሆናል።

እስከዛሬ ድረስ አግላይና ተከፋፍሎ የሚገኝ የፖለቲካ አካሄድ በሀገራችን ህዝብ አንድነትና የነጻነት ትግል ላይ ያሰከተለውን አሉታዊ ተጽእኖ ሁሉም የሚረዳው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሰፊ አለመተማመንና ጥርጣሬን በወገኖቻችን ውስጥ ዘርቶ ይገኛል። ለግፈኛው ስርአት እድሜ መራዘምም ረድቷል። ይህን ለመስበር እና መተማመንን እንደገና ለመገንባት ሰፊ ስራ መሰራት ይኖርበታል። ለዚህም የድብቅብቆሽ ፖለቲካ ተላቆ በትግስት በግልጽነታና ባርቆ አሳቢነት፤ በሰጥቶ መቀበል መንፈስ መስራት አስፈላጊ ነው።

ሰሞኑን በአሜሪካና በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች ቁጥራቸውና ስማቸው የበዛ የፖለቲካና የብዙሃን ድርጅቶች ለየአገራቱ መንግሥታት የድጋፍ መጠየቂያ ሰልፍ ለማድረግ እየጣሩ መሆናቸውን እናያለን። ሽንጎም የዚሁ እንቅስቃሴ አከል በመሆን ይንቀሳቀሳል፡ ከድርጅት ጉድጓዱ ወጥቶ በአንድ ላይ በሰልፍ ድምጽን ማሰማቱ ተገቢና አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንም ይህ ብቻ መፍትሔ ያመጣል ማለት ግን አይደለም። መፈትሔ እንዲመጣ፣ችግሩ እንዲወገድ ከተፈለገ በአደባባይ ለመውጣት የሚሹት የተለያየ ድርጅቶች ከሰልፍ ባሻገር በአገር ቤት ካሉት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ትግሉን ሊመራና ሊያቀናጅ የሚችል ግብረሃይል መፍጠር ይገባቸዋል። በተቃዋሚው ጎራ ብቻ የተሰለፈው ሳይሆን በመንግሥታዊ ዘርፍም ውስጥ የተሰለፈ ግን ስርዓቱ መለወጥ አለበት ብሎ የሚያምን ዜጋ የዚሁ ሕዝባዊ ትግል  አካል ሊሆን ይገባዋል። የሰው ህይወት እስካላጠፋና ሕዝብ እስካልበደለ ድረስ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሰርተሃል ተብሎ ሊገለል አይገባም።ወንጀል የፈጸመውም ቢሆን በማስረጃ በሕጋዊ መንገድ ሊጠየቅ ይገባል እንጂ በደም ፍላት ጥቃት ሊደርስበት አይገባም። ብሄራዊ መግባባትና አገራዊ እርቅ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡ ያ ካልሆነ አሁንም ዞሮ ዞሮ ዜሮ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ለዚህ ወሳኝነት ላለው አደረጃጀትና  ትግል  ተባባሪና ደጋፊ መሆኑን አሁንም በድጋሚ ሊገልጽ ይወዳል።

ለእውነተኛ ለውጥ በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ግንባር ወሳኝ ነው።በጥቂት የውጭ አገር መንግስታትና ድርጅቶች እርዳታና ድጋፍ ሃይል አደራጅቶ ሥልጣን ለመያዝ ከመሯሯጥ ይልቅ በራስ ሕዝብ ፍቃድ፣ተሳትፎና ድጋፍ ለውጥ ማምጣት ከመቅለሉም በላይ የሚያስከብርና የሚያኮራ ነው።

የምንሻው ለውጥ ከሳት ወደ እረመጥ ወይም  ከድጡ ወደማጡ እንዳይሆን እንጠንቀቅ!!! 

ለመሰረታዊ ለውጥ ሁሉንም ያሳተፈ የተቀነባበረ የጋራ ትግል ወሳኝ ነው!! 

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

Hits: 1873

በወገኖቻችን ላይ የሚካሄደው አፈናና ጭፍጨፋ ባስቸኳይ ይቁም

በPDF ለማንበብ ይህን ይጫኑ

በአለፉት  ሳምንታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በመሀል፣  በምእራብ፣ ምስራቅና ደቡብ ምእራብ ኢትዮጽያ የስርአቱን ፖሊሲዎች በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ተማሪወች በገዥው ወያኔ ኢህአዴግ ጸጥታ ሀይሎች መደብደባቸው፣ መታሰራቸውና በጭካኔ መገደላቸው በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች በመገለጥ ላይ ነው።

ወያኔ ኢህአዴግ ላለፉት 24 አመታት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ሰላማዊ ተቃውሞን በሀይል ለማፈን መሞከሩ በሀገራችን ውስጥ አላስፈላጊ የሆነ መካረርን ከማስከተሉም በላይ የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች እጅግ ወደተወሳሰበ ደረጃ ያደርሰዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ በገዥው ቡድን ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለዘመድ አዝማድ  እንዲሁም ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ የተሰማውን  ሀዘን እየገለጠ በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ለማስከበር ሁሉም ኢትዮጽያውያን የሚያካሂዱትን ትግል በጉልበት ለማፈን የሚደረገውን ሙከራ ሁሉ በጥብቅ ያወግዛል።

የሀገራችን ዘርፈብዙ ችግሮች በትእግስት፣ በመደማመጥ፣ ባርቆ አሳቢነትና ለህግ በመገዛት እንጂ በጉልበትና ባፈና ሊፈታ እንደማይችል ገዥው ቡድን ሊገነዘብ ይገባዋል። ትላንት ከትላንት ወዲያ እንደተደረገው ሁሉ ዛሬም የዜጎችን ደም በማፍሰስ በማሰርና በማሰፈራራት ተቃውሞን አፍኖ የስልጣን እድሜን ለማራዘም መሞከር እጅግ ሀላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን፣ ፈጽሞ ማስተዋል አለመቻልም ነው። ገዥው ቡድን በህዝብ ላይ የሚያካሂደው አፈና ሁሉ እንዳልሰራ በተገነዘበ ቁጥር እጅግ ዘግናኝ ወደሆነ ተጨማሪ ተግባር እያመራ ይገኛል። አሁን ያለው ሁኔታ ወገኖቻችንን በገዥው ቡድን የጸጥታ ሀይሎች እጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ሊጠብቃቸው እንደሚችል ያመላክታል።

በድጋሚ የስርአቱ መሪዎች ከዚህ የወንጀል ተግባር እንዲታቀቡ ፣ በህዝብ ላይ ለደረሰው ጭፍጨፋና ስቃይ ተጠያቂ የሆኑ ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ እያሳሰብን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አንዱ ዜጋ ሲነካ ሁሉም እንደተነካ በመገንዘብ የስርአቱን የግፍ እርምጃ በጋራ እንዲያወግዙና በጋራ እንዲቋቋሙ ከማንኛውም ጎራ ለሚመጣ የከፋፋይ ሴራ ሰለባ እንደይሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የተቃወሚ ድርጅቶችም ሆኑ የሲቪክ ማህበራትም ታራ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ከመሯሯጥ ይልቅ ሀገራችንና ህዝባችን ያሉበትን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ተገንዝበው የህዝባችንን አንድነት አጠናክሮ የሀገራችንን ደህንነት አደጋ ላይ ሳንጥል የስርአት ለውጥ ለማምጣት የህዝባችንን ትግል ማቀነባበር የሚቻልበትን መንገድ ባስቸኳይ ለመፈለግ በጋራ እንድንነሳ የትብብር ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

 

Hits: 2001

ብሄራዊ መግባባትና መልካም አስተዳደር “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” መሆን የለበትም!!

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ (ሽንጎ) በሀገራችን ውስጥ የሚታየውን አስከፊ ሁኔታ ቀይሮ አንድነቷ በተጠበቀ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሰው ከፍራቻና፣ ከሰቆቃ ተላቆ መብቱ ተረጋግጦ ፣ እንዲኖር እነሆ ትግሉን ከጀመረ ውሎ አድሯል።

ይህን ራእይ ተግባራዊ ለማድረግም ህዝብን ያማከለ፣ ሰላማዊ፣ ትግል የማካሄድ፣ አስፈላጊነትን አምኖ ይሀንኑም በራእይ ደረጃ አስቀምጧል። ከዚህም አልፎ ታቃዋሚው በሀገር ቤት ወይም በውጭ ሀገር የሚገኝ በሚል አላስፈልጊ ክፍፍል ወይም መሰረታዊ ባልሆኑ የልዩነት ነጥቦች ላይ በማተኮር ራሱን እና አጠቃላይ ትግሉን ከሚጎዳ አካሄድ ተቆጥቦ፣በጋራ ለመቆም የሚያሰችለው የትግል አንድነት እንዲፈጥርና አቅሙንም እንዲገነባ  ደግመን  ደጋግመን አሳስበናል።

አሁን ባለው ሁኔታ ሽንጎ ትልቁ የአንድነት ሀይሎች ስብስብ ቢሆንም አሁንም ገና ወደአንድ ጎራ ሊሰባሰቡ የሚገባቸው እጅግ ብዙ ድርጅቶች፣ስብሰቦችና ግለሰቦች እንዳሉ ግልጽ ነው። ይህን ሃይል አሰባስቦ አይበገሬ ያንድንት ሀይል መፍጠርና ትግሉን ማፋፋም፣ እያደር ወደተወሳሰብ ጎዳና በማምራት ላይ የምትገኘውን ሀገራችንንና ህዝባችንን ለመታደግ ዋነኛው መሳሪያ ነው። ይህ መሰረታዊ ዋሰትና ሳይዘገይ ተግባራዊ እንዲሆንም አሁንም ሳንታክት ጥረታችንን እንቀጥላለን።

የትግላችን  ራእይ የግፍ እና የኣድልኦ ስርአት አክትሞ፣ የህግ የበላይነት፣ ሰብአዊ መብት፣ የሁሉም ዜጋ የግልና የጋራ መብት የሚከበርበት በሁሉም ባለድርሻዎች ሙሉ ተሳትፎ የዳበረ ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲአዊ ስርአትን እውን ማድረግ ነው።

ሽንጎ ደግሞ ደጋግሞ እንደገለጸው እና ባለፈው ነሀሴ ባካሄደው ጉባኤው እንዳጸደቀውም፣ የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት፣ የሁሉንም ዜጎች አወንታና ታአማኒነትን ያገኘ ስርአት ለመመስረት ሀገራችን ያላት አማራጭ በብሄራዊ መግባባትና በብሄራዊ እርቅ ጎዳና መጓዝ ነው።

ይህ ሂደት ካግላይነት የተላቀቀ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳተፈ፣ የሁሉንም ድምጽ ለማዳመጥ፣ የቆረጠ፤ ለጋራ ችግራችን የጋራ መፍትሄን ለመፈለግ የሚያስችል መሆን ይገባዋል። በኛ አመለካከት ብሄራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ የተወሰኑ ክፍሎች ወይም ድርጅቶች ከደረሰባቸው ውጥረት ለመወጣት የሚጠቀሙበት የጊዜ መግዣ ታክቲክ ሳይሆን በሀገራችን ውስጥ የሚታዩ ፖለቲካዊ፣ማሀበራዊና ሌሎችንም ችግሮቻችንን ፊት ለፊት በጋራ መርምረን በአርቆ አሳቢነት፣ በብሰለትና፣ በመቻቻል፣ በወንድማዊና እህትማማች ስሜት፣ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት  የጋራ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረግ እውነተኛ ጉዞ ነው መሆን ያለበት።

ይህ ሲሆን ብቻ ነው ለዘላቂ ሰላም፣ ለልማት፣ ለምንመኛት ታላቅ የበለጸገች ኢትዮጵያ መሰረት የምንጥለው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው፣ አላስፈልጊ ደም መፋሰስን፣ የእርስ በርስ መጠፋፋትን ፣ የንብረት መውደምን፣ ስደትን፣ ጽንፈኛነትን፣ ቂም በቀልን አስወግደን ከራሷ ጋር የታረቀች ፣ የጦርነት አዙሪትን የሰበረች ከውጭ ሊሰነዘር ለሚችል ጥቃት ያልተጋለጠች ፖለቲከኞች ከስልጣን በተወገዱ ቁጥር፣ለእስር ወይም ለስደት የማይዳረጉባት ንብረታቸው ከሀግ ውጭ የማይነጠቅባት፣ሀገርና፣የፖለተካ ስርአትን ለመመስረት የሚያሰችል መሰረት የምንጥለው።

በዚህ አንጻር ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የገዥው ህወሀት/ኢህአዴግ መሪ ጠቅላይ ሚኒሰተር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ መንግስታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የነጻ ፕሬስን መብት ለማክበርና ከተቃዋሚዎች ጋር በሀገሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለመመካከር ፍላጎት እንዳለቸው ፣ሌሎችም በህጋዊነት እንዲንቀሳቀሱ ሲሉ ተናግረዋል።

በሸንጎው አመለካከት አሁን በስልጣን ላይ ያለው የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት የችግሩ አንዱ አካልና ዋናው መሠረት በመሆኑ የሀገራችንን የተወሳሰበ ሁኔታ ለብቻው ሊቀይረው ከቶውንም አይችልም፡፡ እንዲያውም አሁን ባለው መልኩ እየቆየ በሄደ ቁጥር የሚወስዳቸው እርምጃወች ችግሩን ወደባሰ መወሳሰብ ያሳድገዋል። በሀገራችን ውስጥ  ጎልተው ከሚታዩት ብሶቶችና ጥያቄዎች አንጻር ሲታይ አንድ ድርጅት በተናጠል ልዩ  መፍትሄ አምጥቶ ሁሉንም ሊያረካ አይችልም።ይህ ቢሆን ኖሮ የህወሀት/የኢህአዴግ የ24 አመታት ጉዞ የኢትዮጵያን ችግር በፈታው ነበር።

የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች በትክክል መረዳት እና  መቅረፍ የሚቻለው ለጥቂት ሰአታት በጠባብ አጀንዳ ላይ ለተቃዋሚዎች ገለጻ በመስጠትና  በገዥው ቡድን እቅድ ላይ “ሀሳባችሁን አካፍሉን “ ወይም “ወደሀገር ተመልሳችሁ ስሩ” ከሚል ንግግር ባሻገር ሁሉንም አሳታፊና እውነተኛ  በሆነ ብሄራዊ መግባባትን እውን ሊያደርግ በሚችል ሂደት ነው።

በሀገራችን ውስጥ የሚታየውን አይነት  የተወሳሰበ ችግር መፍታት የሚቻለው አንዱ መፍትሄ ሰጭ ሌላው ደግሞ መፍትሄ ተቀባይ በሚሆኑበት አካሄድ ሳይሆን ሁሉም የችግሮቹ ባለቤት ሁሉም ደግሞ የመፍትሄዎቹም ባለቤት ሲሆኑ ነው። የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች  መፍታት የሚቻለው ፍትህን፣ መተማመንና፣ አርቆ አሳቢነትን መሰረት አድርጎ ያለፉ ችግሮች እንደገና እንዳይደገሙ ምን መደረግ እንዳለበት  ዋና ዋና በሆኑ ጉዳዮች ላይ በግልጽ ተነጋግሮ መግባባትና መስማማት ላይ መድረስ ሲቻል ነው።

ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ቦታ ሊኖራት ይገባል፤ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያው ቅሬታ፣ የሚደመጥባት፣ መፍትሄም የሚፈለጋባት ልትሆን ይገባል። ኢትዮጰያ በዜጎቿ መካከል የበኩር ልጅ እና የእንጀራ ልጅ የሚባለው አይነት አድልኦ ለማስተናገድ የማትመች መሆን አለባት።ኢትዮጵያ አንዱ ሌላውን “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ፣ ከቻላችሁ ሞክሩን” የሚባልባት ሀገር መሆን የለባትም።

ይህን እውን ለማድረግም ማንንም ያላገለለ ሁሉም ባለድርሻዎች በሚሳተፉበት የብሄራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ ሂደትን እውን ማድረግ ይጠይቃል።ይህ ሂደት ድፍረትን የሚጠይቅ ነው። ሀገሪቱንና ህዝቧን አሁን ወደሚገኙበት ውስብስብ ሁኔታ ካደረሳቸው አካሄድ መላቀቅን የግድ ይላል። ይህ ሂደት በዜጎች መካከል ፣ በተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች መካከል፣ ወዘተ እምነትን መገንባትን እና እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ያሁኑ “ጥሪም” የፖለቲካ ጊዜ መግዣ  አለመሆኑን ማረጋገጥን ይጠይቃል። ይህን ሁኔታ የሚጠይቀውን የመተማመን መሰረት ለማጣል ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁትን የፖለቲካ እስረኞች ጋዜጠኞች ወዘተ መፍታት ለነጻ ፕሬሱና አሁን በህጋዊነት ተመዝግበው በመስራት ላይ ለሚገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ የመፈናፈኛ ሜዳውን ማመቻቸት አንድ ታላቅ እርምጃ ይሆናል።

ይህ ባልሆነበት “ኑ ተሳተፉ;  ምክክር እናድርግ” ማለቱ “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” በሚለው በሀገራችን ብሂል የሚገለጥ ይሆናል።ይህ ደግሞ የሀገራችንን ችግር ከመቅረፍ ይልቅ ይበልጥ ያባብሰዋል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ

Hits: 1766