የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ [ሸንጎ] ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ

home

ዳግማዊ ጴጥሮስ

  

በዛሬው እለት ከጎንደርና ከጎጃም በኩል ዘልቆ የደረሰን ዜና በሁለቱም ክፍለሃሮች ውስጥ                                                         

 

 

 

ዳግማዊ ጴጥሮስ

በዛሬው እለት ከጎንደርና ከጎጃም በኩል ዘልቆ የደረሰን ዜና በሁለቱም ክፍለሃሮች ውስጥ የሚገኙት የሃይማኖትአባቶች፣ቀሳውስቶችና ዲያቆናት  በአዲስ  አበባው  ጳጳስና  ሲኖዶስ  የማይመሩ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።ባወጡት ዝርዝር መግለጫ በአገራችን ላይ የሰፈነውን  ዘረኛ መንግሥትና በሕዝቡ ላይ በመፈጸም ላይ የሚገኘውን  እልቂትና  ጭፍጨፋ፣ማሳደድና  ማሰር አጥብቀው የሚቃወሙ እንደሆነ አስምረውበታል። “ፈጣሪ ከደካሞችና ከሚጠቁት ጎን ተሰለፉ” የሚለውን መሪ ቃል በማውሳትም ማንኛውም የሃይማኖት መሪ ይህን የፈጣሪ ትእዛዝ መቀበልና መፈጸም  እንዳለበት  አሳስበዋል፤የነሱም  መንገድ  ይህንኑ  የሚያበስርና  የጀግናውና  አገር   ወዳዱ የአቡነ ጴጥሮስን አርማ የተሸከመ እንደሆነና የሚመጣውን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን፣ደረታቸውን ለመትረየስ  አንገታቸውን  ለገመድ  አሳልፈው  ለመስጠት  ቆርጠው  እንደተነሱ    ዘክረዋል።

በሌላም በኩል የኢትዮጵያ ሙስሊም እምነት ተከታዮች ከኢድ አረፋ በዓል ጸሎት በዃላ በየመስጊዶቻቸው የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ ውለዋል።በድረዳዋም አደባባይ ወጥተው ወያኔን አውግዘዋል።የከተማው አስተዳዳሪ ከንቲባ ለመናገር ሲዘጋጅ ከመድረኩ ላይ  አውርደውታል። ሙስሊሙ በሃይማትና በዘር መከፋፈል ተገቢ እንዳልሆነ በማውሳት በዚህ መልክ መሄድን አውግዘዋል።በዚሁ ሰላማዊና ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ እንደተለመደው የስርአቱ ጠባቂ የሆኑት የታጠቁት አውሬዎች የተኩስ እርምጃ ወስደው የብዙ ንጹህ ወገኖቻችን ደም እንደፈሰሰ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ በሁለቱም የሃይማኖት አባቶችና ተከታዮች የተወሰደው አገር አድን፣ ጸረ አምባገነንና ጸረ ዘረኛ ትግል በእውነትም የፈጣሪያቸውን ትእዛዝ የተከተለና አክብረው ለማስከበር እንደሆነ ያምናል፤ያደንቃልም።ይህን የአባቶቻችንን ድፍረትና ወኔ ብሎም አገር ወዳድ አቋም በሌላውም አካባቢ ያሉት የሃይማኖት ተከታዮች እንዲከተሉና ተመሳሳይ አቋም እንዲያዙ ጥሪ ያደርጋል።የአክሱም ጽዮን፣የላሊበላ፣የግሸን ማርያም፣የዝቋላ፣ የቁልቢ ገብርኤል፣የአዲስ አበባ አድባራትና የቀሩትም የጎንደርና የጎጃም ሊቃውንትና የሃይማኖት መሪዎች የዳግማዊ ፔጥሮስን መስቀል ተሸክመው ላገራቸውና ለወገናቸው ክብር፣አንድነትና ነጻነት የወሰዱትን አቋም እንዲከተሉ ጥሪ ያደርጋል።በተለያዩ ያገራችን ክፍሎች የሚገኙት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችም እንደ ጎንደር፣ጎጃም፣አዲስ አበባውና ድሬዳዋው ጀጎኖች ሙስሊሞች ከሃይማኖትና ከዘር ፖለቲካ ነጻ የሆነች አገር እንድትመሰረት   የሚሻውን ተመሳሳይ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ ያደርጋል።
በውጭ አገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናት መሪዎችና ምእመናን፣ በአመስተርዳም ከተማ በሚገኘው በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምእመናን የተወሰደውን  አቋምና እርምጃ እንዲከተሉና ትግሉ ሁሉን አቀፍና ዓለም አቀፍ እንዲሆን ጥሪ ያደርጋል። በአመስተርዳም ምእመናን  የተካሄደውን  ክርስቲያናዊ  እርምጃ  ከልብ  ያደንቃል።
 
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ በክርስቲያኑና በሙስሊሙ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውንና የሚፈጸመውን ማንኛውንም እርምጃና ወንጀል በሚችለው መንገድ እያጋለጠ ወንጀለኞቹ ለፍርድ የሚቀርቡበትን  መንገድ  እንደሚያጠና  ሊያረጋግጥ  ይወዳል።

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!! ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

Hits: 1623

በማስፈራራትና በዛቻ የሕዝብ ትግል አይቆምም

ቢሆን ይሆናል ባይሆን አይተነው፣
  እንሄዳለን አደባይተነው።                      

 

በማስፈራራትና በዛቻ የሕዝብ ትግል አይቆምም

ቢሆን ይሆናል ባይሆን አይተነው፣

እንሄዳለን አደባይተነው።

በዚህ አይነቱ ስንኝ የታጀበ የእልቂት ፉከራና ዛቻ አባይ ጸሃዬና ስዩም መስፍን የተባሉት ቀንደኛ የሕወሀት ወንጀለኞች በብዙሃን የመገናኛ መድረክ ላይ ከ40 ደቂቃ በላይ በሰጡት ማብራሪያ የተደመጠ የሰሞኑ የሽብር መልእክት ነበር።እነዚህ የሕዝብና የአገር ጠላቶች ድርጅታቸው በሚመራው መንግበሥት ላይ የደረሰውን የፖለቲካና ማህበራዊ ክስረት ተመርኩዘው ካደረባቸው ስጋት በመነሳት ሕዝቡን ያልነቃ፣ዃላ ቀርና ለውጭ ሃይሎች ያጎበደደ ያቀጣጠለው ግርግር ነው ብለው የስድብና የንቀት ናዳ ሲያወርዱበት፣ የሕዝቡን እሮሮ የሚያጋልጡትንና የሚታገሉትን በውስጥና በውጭ የሚገኙትን የለውጥ ሃይሎችን እንደማንኛውም አምባ ገነን ስርዓት ጥላሸት እያለበሱ ከጥያቄው ለማምለጥ ሲውተረተሩ ተደምጠዋል ። የነፍጠኞች፣ የትምክህተኞች፣የጠባቦችና የውጭ አገር ሴራ አስፈጻሚዎች በማለት ከሰዋል።በዚህም ብቻ አላቆሙም እራሳቸውን የአንድነት፣የሰላም፣የእድገት፣ የእኩልነት፣የዴሞክራሲ  ጠበቃና  ፈጣሪዎች  እንደ ሆኑ አድርገው አቅርበዋል። እነሱን መቃወም ማለት ደግሞ ሰላም ማናጋት፣እድገትን መጎተት፣አንድነትን ማፍረስ፣እኩልነትን ሽሮ አንዱ ጌታ ሌላው ባሪያ የሚሆንበትን ስርዓት መልሶ ለማምጣት  የሚደረግ አድማና ሴራ ነው በማለት ጥፋቱን ከራሳቸው ላይ አውርደው በሌላው ላይ ለመጫን ሞክረዋል።ለመሆኑ እድገት ሲባል የሕዝብ አስተያየትንና ንቃትን ያካተተ አይደለምን? ሕዝቡን ዃላ ቀር፣ደደብ ብለው ከተሳደቡ በሕዝቡ ንቃት ለውጥ አልመጣም ማለት ነው።

አደገ ተመነደገ የሚሉት ኤኮኖሚ ከሕንጻና ከከበርቴው መዝናኛ ቦታዎች  መስፋፋት  ያለፈ  አይደለም ማለት ነው።የውጭ ዘራፊዎች ካቋቋሙት ድርጅት የዘለለ ለውጥ በአገሪቱና በሕዝቡ ኑሮ ብሎም ግንዛቤና ንቃት ላይ አላመጣም ማለት ነው። እውነተኛ እድገት አለመኖሩን በደም ፍላት ያስተላለፉት መልእክት ፈልቅቆ አወጣው።ከአፍ ከወጣ አፋፍ! ይሏል ይህ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለበትን ኑሮና መከራ እያወቀውና እየተቃወመው ጥያቄና ቅዋሜውን ከዃላ ቀርነት፣ ከድንቁርናው የመነጨ ድክመት ነው በማለት የሕዝብን ችሎታ በማኮሰስ የሚያደርገው ትግልም የደደቦች ተግባር ነው በማለት አርክሰውታል።ሕወሀት ንቀትና እብሪት በዛሬው በነዚህ ሁለት ጨካኞች የተጀመረ ሳይሆን የፈጠሩት ድርጅት ከተመሰረተበት ከዛሬ አርባ ዓመት ጀምሮ ሲዳብር የኖረ፣አሁን አገራችን ካለችበት ውድቀትና አደጋ ውስጥ የነከረ መመሪያና ስልት ነው። አገርን ለመበታተን፣የሕዝቡን አንድነት ለማናጋት ዘርን፣ ሃይማኖትን፣ቋንቋና ክልልን መሳሪያ አድርጎ የተጠቀመው ህወሃት/ኢህአዴግ እንጂ ሕዝቡና ለዴሞክራሲ ለውጥ፣ለፍትህና ለእኩልነት የተነሳው ሕዝባዊ ሃይሉ እንዳልሆነ እነሱም ሌሎቹም ያውቁታል።ሕዝባዊ ሃይሉ ችሎ ችሎ የግፉ መጠን ገደቡን ሲያልፍ በቃኝ ብሎ ተነስቷል፤ይህን የሕዝብ
 
መነሳሳት ለመቅጨት እነዚህ ሁለቱ አንጋፋ ወንጀለኞች የድርጅታቸውን የማስፈራሪያ በትር መዘው ብቅ አሉ፣ያም እኛ ከሌለን አገር አትኖርም፣እኛ ከሌለን እርስ በርሳችሁ እንደ ሩዋንዳና ዩጎዝላቪያ ትተራረዳላችሁ፣እንደሶማሊያ ትበታተኑና የትርምስና የእልቂት ሜዳ ትሆናላችሁ፣ልታንሰራሩም አትችሉም የሚል አረመኔያዊ ትንቢት መሳይ ማስፈራሪያ ነው።

ከቀውሱ ውስጥ ግን እራሳቸውን አልቀላቀሉም፤ምክንያቱም ፈርጥጠው ሊወጡ የሚችሉበትን ቦታና በር አመቻችተዋልና! ከዛም በተረፈ በስሙ ተጠቅመው ስልጣን ላይ ወጥተው በአውሬው ክርናቸው የሚደቁሱትን የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ነጥለው በመሳሪያነቱ ለመቀጠል እንዲችሉ የሽብር ቅስቀሳ አድርገውበታል።ብዙሃኑ የትግራይ ሕዝብ በጎሰኛ አስተሳሰብ ተነሳስቶ በሌላው ወገኑ ላይ እንዲነሳና ለነሱ የጥፋት ስርዓት አገልጋይ እንዲሆን አሁንም በዚህ መልእክታቸው አስተጋብተዋል።

በተለያዬ አጋጣሚ እንዳሳየው ሁሉ አሁንም የትግራይ ሕዝብ ዝም ሊላቸውና ለውጥናቸው ተገዢ መሆን አይኖርበትም፤ወግዱ፣አልታለልም፣የእስከዛሬው ይበቃል ሊል ይገባዋል።ህወሃት ያዘጋጀው መቅሰፍትና የጥፋት አደጋ የትግራይንም መሬትና ተወላጅ የሚምር አይደለም።ተያይዞ ገደል እንዳይሆን ይህን በስማቸው የሚነግድ የአገር ፍቅርና ሰብአዊ ስሜት የሌለው ጨካኝ ቡድን ቦታና ዕድል ሊነፍገው ይገባል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲባል የትግራይን ሕዝብ የሚነጥል አይደለም።የኢትዮጵያ ሕዝብ ተበደለ ሲባልም፣ በስርዓቱ ያልተበደለና ያልተሰቃዬ ባለመኖሩ የስርዓቱ አገልጋይ ያልሆነ የትግራይም ተወላጅ የሚጋራው ዕጣፈንታ ነው።የተጨቆነው ሕዝብ ጥያቄው አንድ ነው፤ያም ግፈኛው ስርዓት እንዲያከትም የሚጠይቅና የሚታገል ነው።

በዚያ የነጻነት ትግል ጎራ ውስጥ የትግራይም ተወላጆች አሉበት። ብዙሃኑ ከአጥፊው ቡድን ጋር ሳይሆን ከትግሉ እንዲቀላቀል የሚያደርግ ስራ በስፋት መሰራት አለበት።የወንጀለኞች መጠቀሚያ እንዳይሆን የሚያግዝ ስልት መነደፍ ይኖርበታል።ህወሃት የሕዝቡን አንድነት ለማኮላሸት በሌሎች አሳቦ የሚስጥር ጥቃት በትግራይ ተወላጆች ላይ እንደሚያዘጋጅና እስከመፈጸም ሊጓዝ እንደሚችል ከወዲሁ መገንዘብና ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው።ከአጥፊው ቡድን ጋር ወግነው የሚቆሙት ከማንኛውም ማህበረሰብና ጎሳ የተውጣጡ የስርዓቱ ተጠቃሚዎች የሆኑት ብቻ ናቸው።ጥቅም አይንና ህሊናን ይሸፍናልና በዚያ መጋረጃ ውስጥ ተተብትበው የተያዙት የሁሉም ጎሳ ተወላጆች ናቸው፤ካለነርሱ ትብብር ህወሀት/ኢህአዴግ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ምድር ላይና በሁሉም ሕዝብ ጫንቃ ላይ የመከራ ቀንበሩን ሊያሰፍር አይቻለውም ነበር።

የህወሓት/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት አገራችንን ለሩዋንዳና ለዩጎዝላቪያ እልቂት እያዘጋጁዋት መሆኑን በገሃድ ተናግረዋል፤ኢትዮጵያ በነዚህ አናሳ ወንጀለኞች ውሳኔ የምትፈራርስ ሳይሆን በሕዝቡ የቆረጠና የተባበረ ትግል ለዘለዓለም ተከብራ የምትኖር አገር መሆኗን ማሳየት አለብን። በነሱ የጥፋት ፉከራና ዛቻ ቅስማችን ሊሰበር አይገባውም፤የሕዝቡ ትግል ፈሩን ሳይለቅ፣ከተዘጋጀው የመጠፋፋት ወጥመድ ውስጥ ሳይገባ፣ ለዘላቂ ዴሚክራሲያዊ ስርዓትና የሕግ የበላይነት፣ለሕዝብ አብሮ መኖርና ለአገር አንድነት የምናደርገውን ትግል በተቀናጀ መልኩ ከግቡ ማድረስ የየአንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ድርሻ ሲሆን ይበልጥ ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩን እንለውጣለን ብለው የተሰለፉት ሃይሎች አላፊነት ስላለባቸው  ተባብረው ሊቆሙ ይገባቸዋል፤እርስ በርስ እየተናቆሩ የሚጓዙበት ጊዜው አልፏል፡፤እንደ ህወሓት/ኢሕአዴግ ስርዓት ሰሚ አልባ ላለመሆን ከተፈለገ በትናንትናው የጎሳና የክልል ድርጅታዊ አባዜ መንጎድ የለብንም፤አገራችን
 
ከዚህ አደገኛ ደረጃ ላይ የደረሰችውና ለበለጠም አደጋ የምትጋለጠው በጎሳና ክልል ስሜታዊ አወቃቀር ተነጣጥለን ከተሰለፍን ነው።

ያ አካሄድ እስከዛሬ ድረስና ለወደፊቱም ሕወሀት/ኢህአዴግ ላዘጋጀልን የጥፋት መቅሰፍት ተመቻችተን እንድንገኝ ያደርገናል። በሰው ልጅነታችን፣በኢትዮጵያዊ ዜግነታችን እጅ ለእጅ ተያይዘን የመጣውን አደጋ ከመታደግ የተሻለ ምርጫ የለንም።የሕወሀት/ኢህአዴግን የጥፋት ቅስቀሳ ወደ ለውጥ አቅጣጫ ልንመራው ይገባል።

በቅርቡ አስራ ስድስት የሚሆኑ በአገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱት ድርጅቶች የሰላምና እርቅ ጉባኤ እንዲጠራ ማሳሰባቸው ይፋ ወጥቷል።እርምጃው ቀና ቢመስልም እነማን እንደሆኑ ዝርዝራቸው ስላልወጣና ስለማይታወቅ ድርጅቶቹ በስርዓቱ ተጠፍጥፈው የተቋቋሙ ወይም የተደቀሉ ይሁኑ አይሁኑ የሚታወቅ ነገር  የለም።በተጨማሪም የሰላም አጋርና ጸር  የሆነውን ለይተው ማወቅና ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ውይይት ላይ የመድረክ፣የሰማያዊ፣የመኢአድና የሌሎቹም አገር አቀፍ ድርጅቶች ህልውናና ተሳትፎ አልታወቀም።በስርዓቱ መዳፍና ፈቃድ የሚሽከረከሩት ብቻ ለይስሙላ የሰላም ውይይት ከቀረቡ ውጤቱ እዛው በዛው ይሆንና ፣አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ሆነው የሚያሳልፉት ውሳኔ  የቤተሰብ መተቃቀፍ ይሆናል።

በተጨማሪም የሰላሙ ውይይቱ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያበቃ እንጂ በሽርፍራፊ ለውጥ ያለው ስርዓት    እንዲቀጥል    ለማድረግ    እንዳልሆነ    በቅድሚያ    መገንዘብ    ይገባል።    የሰላም    ውይይቱ በሕጋዊነትተመዝግበው የሚንቀሳቀሱት ብቻ ሳይሆኑ በህወሀት/ኢህአዴግ ተፈርጀው የታገዱትና በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራትና የታወቁ ግለሰቦችን፣ የሚያጠቃልል መሆን ይኖርበታል። ያ ካልሆነ ለሚያስተማምን ሰላምና ሁሉን ላካተተ እርቅ አያበቃም።

ለሰላሙ ውይይት በር መክፈቻው የታሰሩትን መልቀቅ፣የታፈነው የሚዲያ ነጻነት መረጋገጥ፣የመደራጀትና የመሰብሰብ፣የዲሞክራሲ    መብቶች    መከበር፣በሕዝቡ    ላይ    የጥቃት    እርምጃ    እንዲፈጽም    የተሰማራው የመንግሥት የጦር ሃይልና የታጠቀ ቡድን ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲመለስ ፣ጉዳት ለደረሰባቸው ካሳ እንዲከፈላቸው፣  ተጠያቂው  በሕግ  እንዲጠየቅ  ማድረግ  ለነገ  የማይባል  የሂደቱ  መግቢያ  ቁልፍ  ነው። እቅዱ በሕዝቡ ተሳትፎና ፍላጎት እንጂ በጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶችና በቀውሱ ባለቤት በሆነው አምባገነን ቡድን ፈቃድና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን አይኖርበትም።

ስለሆነም የውስጥና የውጭ የሚለው ግድግዳ ተንዶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት እንዲሆን ማድረጉ አማራጭ የለውም።አንዱን አቅፎ ሌላውን ማራቅና ማግለል ለ25 አመት ከተመለከትነው ተመሳሳይ የጥፋት አሮንቃ ውስጥ መዳከር ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውንና በመፈጸም  ላይ ያለውን ግፍና ጭፍጨፋ እያወገዘ፣ ወንጀሉን የፈጸሙትና ያስፈጸሙት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ይጠያቃል።ሕዝቡ ለመለያየት የተቀመረለትን የጥፋት ጎዳና እንዳይከተል እያሳሰበ እጅ ለእጅ ተያይዞ ጥቃቱን እንዲመክት ጥሪ ያደርጋል።የሕዝቡን ብሶት ለዓለም ማህበረተሰብ ለማሰማትና በስርዓቱ ላይ ተአቅቦ እንዲጣል ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ እየገለጸ፣በውጭ አገር የሚገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች፣
 
የሲቪክ  ማህበራትና ተቋማት  እንዲሁም  ግለሰቦች  በዚህ  ፈታኝ  ወቅት  ላይ  ከመቸውም ጊዜ  በበለጠ የአንድነት ትግላቸውን ማካሄድና እርዳታ ለሚያስፈልገው ወገናቸው ገንዘብ የማሰባሰቡን ሥራ እንዲቀጥሉበት ጥሪ ያደርጋል።

የተከሰተውን አደጋ ለመመርመርና የአገራችንን የወደፊት አማራጮ ለመመካከር በአስቸኳይ ጉባኤ መጠራት እንዳለበት በማመን ሸንጎ የበኩሉን ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ለማሳወቅ ይወዳል፡፤ በዚህ በታሰበው ጉባኤ ላይ እንዳለፈው ጊዜ ምክንያት እየፈጠሩ  ማፈግፈግ አገራችንና ሕዝቡ የተደቀነበትን አደጋ ጥልቀትና አጣዳፊነት አለመረዳት ይሆናል።አላፊነት የሚሰማቸውና አደጋውን የተረዱ ጥሪውን አክብሮ ከመገኘት ሌላ አማራጭ የለም።ስለሆነም ሁሉም ጥሪውን አክብሮ ይገኛል የሚል እምነት አለን።

የተሰናዳልንን የጥፋት ሴራ በአንድነት እናክሽፈው!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

Hits: 2191

ሕዝብን አፍኖና በኃይል ረግጦ መግዛት ያብቃ!- ህወሓት በአወዳይ የፈጸመውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ሸንጎ አጥብቆ ያወግዛል።

በትላንትናው ዕለት ትንሽ ትልቅ፣ ወንድ ሴት፣  ከተሜ  ገጠሬ፣  ሳይል  የጎንደር  ሕዝብ  ከዳር እስከ ዳር በነቂስ ወጥቶ ከተማዋን ባጨናነቀ መልኩ የህወሓት አገዛዝ የፈጠረውን የሽብርና የፍርሃት አጥር ሰብሮ በመውጣት የተቃውሞ ድምጹን በሰላማዊ መንገድ አሰምቶ ወደቤቱ ተመልሷል። ምንም እንኳን አገዛዙ  የተቃውሞ  ሰልፉ  እንዳይካሄድ  ማናቸውንም እርምጃዎች ቢወስድም፣ ግፍ የበዛበት፣ የቆረጠና የተባበረን ሕዝባዊ ማዕበል የሚመክተው አንዳችም ምድራዊ ኃይል የለምና ከፍተኛ ጨዋነት በተሞላው መልክ ሕዝቡ ተቃውሞውን አሰምቷል። በዕለቱ ካስተጋባቸው መፈክሮች ውስጥ  "በኦሮሚያ  የሚደረገው  የወገኖቻችን ግድያ ይቁም" የሚለው የጎንደር ሕዝብ ምንጊዜም በኢትዮጵያዊነትና በሀገር  አንድነት  ላይ ያለው የሚታወቀውን ጠንካራ አቋሙን  ያሳየበትና  የትግል  አጋርነቱን  በግልጽ ያንጸባረቀበት  ነው።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የሕዝብ መብቶች እንዲከበሩና የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተብዬው እንዲሰረዝ በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ላሰሙ ኦሮምኛ ተናጋሪ  ወገኖቻችን አገዛዙ የሰጠው ምላሽ የሕዝብን  ቁጣ  በኃይል  ለማፈን  መሞከር  ነበር።  በዚህም  ከአራት መቶ በላይ የሰው ሕይወት ጠፍቷል። የሕዝብን  ቁጣ  በኃይል  መደፍጠጥ  እንደማይቻል አገዛዙ የተማረ አለመሆኑን ያለፉት 25 ዓመታት የግፍ አገዝዙ ቁልጭ አድርገው አሳይተውናል።  እስካሁን  በተለያዩ   አካባቢዎች   በተጠቀመበት   ነጣጥሎ   ማዳከምና መምታት በሚለው የማፈኛ ስልቱ በትላንትና ዕለት በምሥራቅ ሐረርጌ በአወዳይ  ከተማ ውስጥ ባካሄደው ጭፍጨፋ በርካታ ዜጎችን ሲያቆስል የስድስት ወገኖቻችንን ሕይወት ማጥፋቱን የተለያዩ የዜና አውታሮች ዘግበዋል። ህወሓት በጎንደር በተካሄደው ሰላማዊ ተቃውሞና ሕዝባዊ ማዕበልን መቋቋም እንደማይችል ምናልባት ተረድቶት  ይሆናል የሚለውን ግምት ውድቅ እንዳደረገው እነሆ በአወዳይ ከተማ የፈጸመው ጭፍጨፋ ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል። በመሆኑም ይህን  ህወሓት  የፈጸመውን  አረመኔያዊ  ድርጊት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ አጥብቆ ያወግዛል።
ጆሮ ያለህ ስማ እንዲሉ የህወሓትን አፋኝ፣  ጨፍጫፊ፣ ዘረኛና አምባገነን ቡድን ማስታወስ የምንወደው በዓለም ዙሪያ የነበሩ አምባገነን አገዛዞች ሁሉ በውርደት ከሥልጣን መወገዳቸውን ቢያንስ የመንግሥቱን፣ የሙባረክን፣ የጋዳፊን፣ የሳዳምን...ወ.ዘ.ተ እጣ ፈንታ እንዴት እንደነበረ ነው። ስለዚህ የሥልጣን ምንጭና  ባለቤት  የሆነውን  ሕዝብ  መብት አፍኖና  በኃይል  ረግጦ  ለዘለዓለም  መግዛት  እንደማይቻል  ተረድቶ  ሕዝብ  ለእልቂት፣ ሀገርም ለበለጠ ጉዳት ከመዳረጓ በፊት መብቱን በሰላም ለጠየቀ ሕዝብ ትክክለኛው ምላሽ እንዲሰጠው ይገባል እንላለን። ይህ ሳይሆን ቢቀርና ህወሓት እስካሁን  በተከተለው  ጎዳና ከቀጠለ ለሚደርሰው የሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም ተጠያቂው ህወሓት ብቻ መሆኑን ከወዲሁ መግለጽ እንወዳለን። ሕዝቡ የሀገር አንድነቱን ጠብቆ መብቱን በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር  የሚያደርገውን  ትግል  የኢትዮጵያ  ሕዝብ  የጋራ  ትግል  ሸንጎ እንደሚደግፍ በማያሻማ ቋንቋ እየገለጸ፣ በሚችለው ሁሉ ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።
አንድነቷ የተጠበቀ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በሕዝብ ትግል ትመሠረታለች!

Hits: 2332

የጎንደር ሕዝባዊ ትግል ኢትዮጵያን የማዳን ትግል ነ ው!!

ሰሞኑን በጎንደር ከተማና አካባቢው የፈነዳው ሕዝባዊ እምቢባይነት ታፍኖ ሲብላላ የቆየው የሕዝብ እንቅስቃሴ ክምችት ውጤት ነው።ይህ ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ትግል ላለፉት አርባ ዓመታት በተለይም ላለፉት 25ዓመታት ሕወሃት የተባለው አገር አጥፊ ድርጅት አገሪቱን ሸንሽኖ፣ ዳርድንበሯን ቆራርሶ ለባእዳን በመስጠትና በመቸርቸር፣ ሕዝቡን በጎጥ ጎራ አሰልፎ እንዲተላለቅና በግርግር የትግራይን ነጻነትና “ትልቋን ትግራይን” ለመመስረት የተነሳበትን ዓላማ    እውን  ለማድረግ ከቋጠረው ሴራ የተወለደ ሕዝባዊ ተቃውሞና እምቢ ባይነት ነው። ዓላማውን ለማሳካትና ትግራይን በራሷ እንድትቆም በሚል ቀቢጸ ተስፋ የአጎራባች የኢትዮጵያ ክፍለሃገር ለም  መሬቶችንና  ሕዝቡን  በሃይል  አስገድዶ  የትግራይን    መሬት ከሚገባው በላይ ለጥጦ ሲከልል፣ ለተነሳበት    ዓላማ መሳካት አያሌ ተንኮሎችን ሲሸርብና ሲዘጋጅ የጎንደር ሕዝብ በዝምታ  አላየውም። የነበረውን ተንኮል ገና ከጅምሩ ለማክሸፍ ያደረገው ትግልና የከፈለው መስዋእትነት  ብዙ ነው፤አሁን በዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ የአገራችንን ሕዝብ ከዳር እስከዳር ያስቆጣና ያነሳሳ    ሕዝባዊ እምቢባይነት የዚያ ጥርቅም ውጤት ነው።ይህ በተለያዩ ያገሪቱ ክፍሎች የተካሄደውና በመካሄድ ላይ ያለው ሕዝባዊ ትግል በደሃውና አገሩን በሚወደው የትግራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ የጥቃት እርምጃ ሳይሆን እራሱን የትግራይን ሕዝብ ቀፍድደው በስሙ ከሚነግዱና ለእልቂት ከሚጋብዙት ባንዳ ተወላጆቹ ቁጥጥር ነጻ ለማውጣት እንደሆነ መታወቅ አለበት።የትግራይ ተወላጅ የሆኑት የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥት አጼ ዩሃንስ አንገታቸውን የሰጡበትና የጦር መሪው ራስ አሉላ አባነጋ እንዲሁም አያሌ የትግራይ ተወላጆች በከፈሉት መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየውን የኢትዮጵያ አገራችንን    ዳር ድንበር በዛው በትግራይ መሬት የበቀሉ አገር አጥፊና ከሃዲ ስብስቦች ኤርትራን ለጣልያን  ቡችሎች፣የጉሙዝና  የቤኒሻንጉልን  አዋሳኝ  ሰፊ  ለም  መሬት  ለሱዳኖች(ለደርቡሾች) አሳልፈው  ሲሰጡ  ማየት  እንኳንስ ለትግራይ  ተወላጅ  ቀርቶ  ለአፍሪካ ነጻነትና  ለኢትዮጵያ  አንድነት የሚቆረቆር አፍሪካዊውን ልብ ያደማል፣ስሜት ይቀሰቅሳል። በስሙ ሥልጣን ላይ የተቀመጡት ከይሲዎች የትግራይ ተወላጅ አሁን በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የሚካሄድ ሕዝባዊ ትግል እንዳይቀላቀል፣ፈርቶ  እንዲሸሽና  በጠላትነት  ፈርጆ  ለመከላከል  ጦር  እንዲመዝ        ያላሰለሰ ቅስቀሳና ጥሪ ፣ብሎም በታጋዩ ሕዝብ ስም የሚያስፈራሩ መልእክቶችን በብዙሃን መገናኛዎች፣ማለትም በፌስቡክ፣በቫይበርና በመሳሰሉት መርዛቸውን እየረጩ ስለሆነ ከወጥመዱ ውስጥ እንዳይገባ፣ከትግሉ ጎራ  እንዳያፈገፍግየኢትዮጵያ  ሕዝብ  የጋራ  ትግል  ሸንጎ  ያሳስባል።በተመሳሳይም  ደረጃ  የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም፣የሕዝቡን ግንኙነትና አብሮ መኖር የማይፈልጉ፣በግርግር ሊጠቀሙ የሚሹ የውስጥና የውጭ አገር ጠላቶች ይህን ሕዝባዊና ሰላማዊ ትግል በመጥለፍ ወደሌላ አቅጣጫ ለመለወጥና ትርምስ እንዲፈጠር የተለያየ ዘዴ መጠቀማቸው ስለማይቀር ሰለባ ላለመሆን ነቅቶ መጠበቅ እንደሚያሻ ሸንጎ ያስገነዝባል። በተጨማሪም በሰላምና እርቅ ስም የተወሰኑ ስብስቦችን  ብቻ ያካተተ፣ሌሎቹን አገር ወዳዶች ያገለለ በውጭ ሃይሎች ምርጫና ግፊት    የጨቋኞችና የዘራፊዎች ስርዓት ዳግም እንዳይንሰራራ ነቅቶ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ    ሸንጎ  ያሳስባል።የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የውጭ ሃይሎች ስላልሆኑ መድረኩንና ውሳኔውን እንዳይቀሙት  መከላከል  ተገቢ  ነው።

ሙሉውን ለማንበብ ይህን ይጫኑ

Hits: 2190

የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባበሩ፤ የታሪክ ግዴታችሁን ተወጡ እያለን ነው!

 

ኢትዮጵያውያን ከባላባታዊ አገዛዝ ተላቀው የነፃነት አየር ለመተንፈስ ሲዘጋጁ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣኑን ከሕዝብ ቀምቶ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ለ17 ዓመታት እያሸበረ ረግጦ ሲገዛ ኖረ። አለመታደል ሆኖ ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ ሆነና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሕዝባችን ሥልጣኑን ተቀምቶ ላለፉት 25 ዓመታት በጠባብ ብሄረተኛውና በዘረኛው በህወሓት አስከፊ የጭቆና አገዛዝ እየተረገጠ ይገኛል። ይህ ጠባብ ብሄርተኛ ቡድን የብሄር ጥላቻን መርዝ እየረጨና እንደ ፖለቲካ መቆያ ስልት እየተጠቀመ አገሪቱንና ሕዝቦቿን ከፋፍሎና አዳክሞ ለአደጋ አጋልጧቸዋል። ዛሬ በአገዛዙ ያልተማረረ ኢትዮጵያዊ ፈልጎ ለማግኘት አይቻልም። በሸንጎ እምነት የሀገራችን ሁኔታ ከመጥበሻው ወደ እሳቱ እንዲሉ፣ በየጊዜው ሁኔታዎች እየተባባሱና አስከፊ እየሆኑ መጥተዋል።
ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብታም ሆና ሳለ ብልሹ አስተዳደሮች በዓለም ደረጃ በድህነትና በረሃብ እንድትታወቅ አድርገዋታል። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ ላሉት ችግሮች ሁሉ አልፋና ኦሜጋው አምባገነናዊ፣ ጠባብ ብሄርተኛውና በሙስና የተዘፈቀው የህወሓት ብልሹ አገዛዝ ነው። ይህ ኪራይ ሰብሳቢ ቡድን አባላቱን ሃብታም እያደረገ  አብዛኛውን  የኢትዮጵያን ሕዝብ በድህነትና በረሃብ አለንጋ ይገርፈዋል። ሕዝብ ለመብቱ ሲነሳ ህወሓት የሚስጠው መልስ ልዩ ኃይል ልኮ ሕዝቡን ማጥቃት ነው። የዚህ አገርአቀፍ የሆነ አስቃቂ የሥርዓት ግፍ መፍትሄው የህወሓትን አምባገነናዊ አገዛዝ ለአንዴና ለሁል ጊዜ በሕዝባዊ ትግል ከሥልጣን ማስወገድና አግላይ ያልሆነ የሀገሪቷን ዜጎች ሁሉ በእኩልነት የሚያሳትፍ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ብቻ ነው። ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያ አንድነትና የተቃዋሚ ኃይሎች በመተባበር በአንድነት፣ በአንድ ቋንቋ፣ በጋራ መታገል ይኖርባቸዋል። በእኛ እምነት መላው ዓለም ተቃዋሚውን ሊያክብረውና  ሊቀበለው የሚችለው በጋራ በሚያገናኘን መለስተኛ  ፕሮግራም ዙርያ በመሰባሰብ  ለአንድ ብሄራዊ ዓላማ ተፈላልጎ፤ ተፈቃቅዶና ተባብሮ ሲነሳ ነው።
ህወሓት፤ በኢህአዴግ  ሽፋን  ሕዝብን  እየረገጠ  የሚገዛው፤  ባለፉት  25  ዓመታት በወገኖቻችን ላይ የፈጸመው ግፍ በሀገራችን አራቱም  ማዕዘናት  የተካሄደ  ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብም ጠንቅቆ የሚያውቀው ሃቅ ነው። ህወሓት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ይጠቅሙኛል ያላቸውን እርምጃዎች ሁሉ ወስዷል። ሰብዓዊና  ዴሞክራሲያዊ  መብቶችን  ረግጧል፣  የነፃውን  ፕሬስ  አፍኗል፣  የሕዝብን  ድምፅ
 
ሰርቋል፣ ኅብረ-ብሄር የሆኑ ተቃዋሚ ድርጅቶችን አፍርሷል፤ በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ድምፃቸውን  ያሰሙ   ወገኖቻችንን  አስሯል፣  ገድሏል፣  ከሀገር  እንዲሰደዱ  አድርጓል፣ እህቶቻችን በዐረብ አገሮች ስብዕናቸው እንዲደፈር አድርጓል፣ ወጣቶች ተሰደው በባህር እንዲሰምጡ፣  በበረሃ  እንዲሰየፉ  አስተዋጽዖ  አድርጓል፣  ሕዝብ  በሕዝብ  ላይ  እንዲነሳሳ መሠሪ የጠብ አጫሪነት ሚና ተጫውቷል፣ ኢትዮጵያዊነትን በመሸርሸር የጎሣ ፓለቲካን አስፍኗል፣ በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ በመግባት ለማጋጨት ጥሯል፣ ኤርትራን አስገንጥሎ ሀገራችንን ያለ  ወደብ  አስቀርቷል፣  የሀገራችንን  መሬት  ቆርሶ  ለሱዳን  ለመስጠት ተስማምቷል፣ ነዋሪዎችን ከቀዬአቸው እያፈናቀለ  ለምና  ድንግል  መሬታችንን ለ"ኢንቬስተሮች" ቸብችቧል፤ በጎንደርና በወሎ መሬቶችን እየነጠቀ ወደ ትግራይ ክልል አጠቃሏል፤ ነዋሪውን ሕዝብ ሳያማክር በብሄርና  በቋንቋ  በማደራጀት  ስም  መሬት  ካንዱ ወደ ሌላው በማካለል ተዋድዶና ተቃቅፎ አብሮ የኖረን  ሕዝብ  ደም  በማቃባት  ሥፍር ቁጥር የሌለው ወገናችን እንዲገደል በማድረግ በኅብረተሰባችን ውስጥ የነበረውን መልካም ግንኙነት እንዲበጣጠስ አድርጓል፣ የአማራውን ሕዝብ እየከፋፈለና እያሳደደ መቆሚያና መኖሪያ አሳጥቶታል..ወ.ዘ.ተ፣ ወ.ዘ.ተ። በአጠቃላይ ህወሓት ለሀገር አንድነት፣ ለልማትና ዕድገት የቆመ አገዛዝ ሳይሆን ዜጎቿን  እየበደለና  እየረገጥ  አፍኖ  በመግዛት  ሀገርን ለማጥፋት ሌት ተቀን ቆርጦ እየሠራ ያለ አምባገነንና  አሸባሪ  አገዛዝ  ነው።  የሀገራችን ችግሮች እምብርትም ችግሮችን በመቀፍቀፍ የሚታወቀውና የዜጎችን መብቶች የሚረግጠው ይኽው አምባገነኑ ህወሓት ነው።
በሃያ አምስቱ የህወሓት አገዛዝ ዘመን በሀገራችን ውስጥ ሰላም ሰፍኖ አያውቅም። በበደኖ፣ በአርባጉጉ፣ በአርሲ፣ በጎንደር አደባባይ ኢየሱስ፣ በሲዳማ፣ በአኝዋክ፣ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች...ወ.ዘ.ተ ላይ የፈጸማቸው ጭፍጨፋዎች ለአብነት ከሚጠቀሱት ጥቂቱ ናቸው። በቅርቡ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሳቢያ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንና በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በጎንደር  እየተካሄድ  ያለው  ግፍ  የሀገራችንን  ሕልውና  አሳሳቢ  ደረጃ   ላይ   አድርሶታል። አገዛዙ ሁኔታዎችን በጥሞና መርምሮ ትክክለኛ መፍትሄ መስጠት ባህሪው አይደለምና ለሕዝብ ጥያቄ እየሰጠ ያለው ምላሽ አሁንም ኃይልን በመጠቀም ፀጥ  ለጥ  አድርጎ ለመግዛት መሞከርን ነው። የሚዘገንነው ደግሞ ማንም የውጭ ኃይል  ጣልቃ  ሳይገባበት በጎንደር ሕዝብ ቆራጥነትና ደፋርነት የሚካሄደው ሕዝባዊ አመጽ “የሽብርተኞች አድማ፤ የኤርትራ መንግሥት እጅ የገባበት፤ የግንቦት ሰባት/አርበኞች  ቅስቀሳ”  እና  ሌላም  ሌላም እያለ የፈጠራ ወሬ ያስተጋባል። የጎንደር ሕዝብ ምንም ያላሰበውንና  ያላደረገውን  ራሱ ፈጥሮ  ሕዝባዊ  አመጹ  “በትግራይ  ተወላጆች  ላይ”  እልቂት  ለማምጣት  ነው  ይላል። የጎንደር ሕዝብ እንደሌላው  የኢትዮጵያ  ሕዝብ  ሁሉ፣  ህወሓት  ወንድሞቹና  እህቶቹ የሆኑትን የትግራይ ተወላጆች የማይወክል መሆኑን ጠንቅቆ የሚያውቅ፤ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን፤ በጨዋነትና በትዕግስት የሚታገል ሕዝብ ነው።  ባጭሩ፤  የተመጽዋችነት ከረጢቱን ለመሙላት የሚጠቀምበትን  ካርድ ብቅ በማድረግ ችግር ፈጣሪዎቹ  አሸባሪዎችና የሻዕቢያ ተላላኪዎች ናቸው በማለት የአብዬን ወደ እምዬ እንዲሉ በሌሎች ላይ ለማላከክ እየሞከር ይገኛል። ይህ ጊዜ ያለፈበት  ብልጣብልጥነት  በኦሮሞያም፤  በኦጋዴንም፤ በጋምቤላም ወዘተ ታይቷል።   ሀቁ ግን ችግር ፈጣሪው እራሱ የህወሓት አገዛዝ ነው።
 
ወልቃይቴዎች ሕገ-መንግሥት ተብዬው በሰጣቸው  መብት  መሠረት  በተለያዩ  ጊዜያት በተለያዩ እርከኖች  ላይ  ለሚገኙት  የአገዛዙ  አካሎች  በሕጋዊ  መንገድ  የማንነት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ይህም ጥያቄያቸው፤ “እኛ አማራ እንጂ ትግሬ አይደለንም፤ የጎንደር አካል እንጂ የትግራይ አካል ለመሆን  አንፈልግም”  የሚል  ነው።  ሆኖም፤ በተጨባጭ ያገኙት ምላሽ ወልቃይቴ ነን ያሉትን ንብረታቸውን መዝረፍ፣ ማሰር፣ ሴቶችን መድፈር፣ መሬታቸውን መቀማት፣ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉትን  አፍኖ  ደብዛቸውን ማጥፋት፣ በሥራ መስክ አድልዖ ማድረግ...ወ.ዘ.ተ፣ ወ.ዘ.ተ ናቸው። ይባስ ብሎ አቤቱታቸውን ለአገዛዙ እንዲያሰሙ ሕዝብ የመረጣቸውን ወኪሎች አስሯል። በሰላም በመወያያት ችግሮችን ለመፍታት የሚጥሩ ወገኖችን ማሰርና ማሰቃየት ለህወሓት አዲስ አለመሆኑን ገና ከጠዋቱ የ1983 ዓ. ም የሰላምና ዕርቅ  ኮንፈረንስ  ላይ  ለመሳተፍ የተወከሉትን የተቃዋሚ ኃይሎች ማሰሩን ልብ ይሏል። ግፍ ሞልቶ ሲትረፈረፍ ሕዝብ መብቱን ለማስከበር ማናቸውንም እርምጃዎች  ይወስዳልና በጎንደርም  እየሆነ  ያለውም ይኼው ነው። በመሆኑም ሥፍር  ቁጥር  የሌለው  ሕዝብ  አልገዛም  ባይነቱን  በግልጽና በአደባባይ እየገለጸ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ፤ የጎንደር ወጣት፤ ሽማግሌ፤  መንፈሳዊ  አባት፤ እናት፤ ሴት፤ ወንድ፤ ሃብታምና ድሃ ሳይለይ  መላው  ሕዝብ  በሕዝባዊ  አመጹ  እየተሳተፈ ነው። በህወሓት ልዩ ቡድን የተገደሉትን የግል ባለ ኃብት ጎንደሬ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ለማክበር የወጣው ሕዝብ “የሦስት ጥምቀቶች” በዓልን ሕዝብ ቁጥር ያካትታል። ይህ ብቻ ሕዝቡ  ቆርጦ  የተነሳ  መሆኑን  ያሳያል።
አሁን ያለው መፍትሄ አንድና አንድ ነው። ኢትዮጵያ፣ የዓለምአቀፉን የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን፣ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርን ፈራሚ ስለሆነች ይህንኑ ስምምነቷን አገዛዙ በተግባር  መተርጎም  ያለበት  ጊዜ ነው። ሀገራችን ወደ አስከፊ የሕዝብ  መተላለቅና  የንብረት  መውደም  ውስጥ  ከመግባቷ በፊት ለአገዛዙም የወንድ መውጫ በር እንዲሉ የሚበጀው አሁን ያለው  ፍጥጫ  ውጤቱ መጥፎ እንዳይሆን የሕዝብን ጥያቄ አዳምጦ በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ መሞከር ነው። ከሕዝቡ ጥያቄ አንዱና  ዋናው  የታሰሩትት  የኮሚቴ  አባላት  ያለምንም  ቅደመ  ሁኔታ መፍታት ነው። ሁለተኛው ሕዝቡን ለማስፈራራት ወደ ጎንደር  የተላከው  የህወሓት  የጦር ኃይል ወደ ካምፑ እንዲመለስ ማድረግ ነው።
አገዛዙ ይህንን ዕድል ተጠቅሞ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ሳይፈታ ቢቀር ለሚደርሰው የሕዝብ እልቂትና የንብረት መውደም ተጠያቂው ሙሉ በሙሉ ህወሓትና ህወሓት ብቻ መሆኑን ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን። በአርቆ አሳቢው ሕዝባችን በኩል ደግሞ አገዛዙ ለሚያሰራጨው የጥላቻና የከፋፋይ ደባ ሰለባ ሳይሆን የሀገርና የወገንን ንብረት በመንከባከብ እስካሁን እንደሚያደርገው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን  በተላበሰ  መልክ  አንድነቱን  አጠንክሮ እጅ ለእጅ ተያይዞ የአገዛዙን ፀረ-አንድነትና ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ቅስቀሳ በማምከን በወንድማማችና በእህትማማችነት መንፈስ በአንድነት በመታገል የአገዛዙና የሆድ-አደሮችን ቅስም በመስበር ትግሉን በማጧጧፍ ወደማይቀረው ሕዝባዊ ድል በሚያመራው ጎዳና ላይ እንዲጓዝ   እናሳስባለን።   በማንኛውም   ሕዝባዊ   እንቅስቃሴ   ውስጥ   አንዳንድ   ጋጠወጦች
 
የሚፈጥሩት አላስፈላጊ ጥፋት ሊኖር እንደሚችል በዓለም ላይ በተደጋጋሚ የታይ ቢሆንም፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሠሩ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች መወገዝ ይኖርባቸዋል። በጎንደር ውስጥ ቤቶችና ንብረቶች ሲወድሙ አንድም ግለሰብ የሰውን ንብረት እንዳይነካ መደረጉ የሕዝቡን ጨዋነት ያስመሰክራል። ይህ ደግሞ ለመላው የዓለም ሕዝብ ከፍተኛ ትምህርት  ነው  እንላለን።
የሀገር ዳር ድንበርን ለመጠበቅና ሕዝብን ለማገልገል የተሰለፋችሁ የመከላከያ ሠራዊትና የፀጥታ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ የወጣችሁ እንደመሆናችሁ መጠን ግዳጃችሁ ሀገርንና ሕዝብን ማገልገል ነው። ከሕዝቡ ጎን ቁሙ እንላለን። ውሎ አድሮ እንደማንኛውም አምባገነን ትቢያ ለሚሆነውን አገዛዝ መጠቀሚያ በመሆን ታሪክና ትውልድ እንዳይጠይቃችሁ ወደ ሕዝብ ጎራ እንድትቀላቀሉ ከአሁኑ እናሳስባለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) በተደጋጋሚ እንዳቀረበው አሁንም የተቃዋሚ የአንድነት ኃይሎች፣ ድርጅቶችና መሪዎች፣ ሀገራችን መዳረሻው ወደማይታወቅበት አዘቅት ውስጥ  እያመራች  መሆኗን  በመረዳት  አዘቅቱ  ውስጥ  ከመግባቷ   በፊት   እንድንታደጋት በጋራ መታገል እንደሚገባን  አሁንም  በድጋሚ  ጥሪያችንን  እናቀርባለን።  ተቃዋሚዎች በሕዝብ የተመረጠ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መመሥረት የሚችሉት የፖለቲካ ውድድር በማድረግ ስለሆነ ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው ሀገር ስትኖር ነውና ተባብረን ሀገራችንን  ከህወሓት  መንጋጋ  እናላቅቃት  እንላለን።  ይህን  ማድረግ  ሳንችል  ብንቀር ታሪክና ትውልድ እንደሚጠይቀን በመረዳት ለዚህ  ሀገር  አድን  ጥሪ  አወንታዊ  ምላሽ በመስጠት  አሁንም በጋራ እንድንታገል ሸንጎ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
በመጨረሻም ሸንጎ ከጎንደር ሕዝብ ጎን መቆሙን እያረጋገጠ፤ የሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት እንዲከበር፣ ዜጎች በሕግ ፊት በእኩልነት እንዲታዩ፣ የዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ዜጎች በማኅበራዊና  በፖለቲካው  ዘርፍ  እኩልነታቸው  እንዲረጋገጥና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትመሠረት የሚታገል  ድርጅት  ነውና  የጎንደር  ሕዝብ መብቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ትግል  ሙሉ  በሙሉ  ይደግፋል፣  ተጠናክሮ እንዲቀጥልም  የድርሻውን  ያበረክታል።  በአንፃሩ  ደግሞ  አገዛዙ  በጎንደርና   በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚያካሂደውን ጭፍጨፋ እስራትና ግድያ ሸንጞ በከፍተኛና በማያሻማ ቋንቋ ያወግዛል።
የተባበረ ትግል የድል ዋስትና ነው! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Hits: 2190