የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ [ሸንጎ] ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ

home

በሕዝብ ደም የሥልጣን ዕድሜ ማርዘም!

ሰኔ 13፣ 2008 (ጁን 20፣ 2016)

በዓለም ላይ ከሚታዩት መንግሥታት ውስጥ ሁለት ዓይነት መንግሥታት ጎልተው የሚታዩ ሲሆን፤ ሁለቱም ወደ ሥልጣን እርካብ የሚወጡበት መንገድ የተለያየ ነው።
አንደኛው በሕዝብ ምርጫና ፍላጎት፣ በዴሞክራሲ መንገድ ሥልጣኑን ለተወሰነ ዓመት የሚረከብ ሲሆን ሌላው ደግሞ በራሱ ፍላጎትና ውሳኔ፣ የሕዝብን ድምፅና ፍላጎት ሳይሰማና ሳይጠይቅ በመሣሪያ ኃይል አስፈራርቶና ደምስሶ የሥልጣኑ ባለቤት የሚሆን ነው።
የመጀመሪያውን የስልጣን ባለቤትነትን የሚከተል የግድ የዲሞክራሲን ሕግና ባህል የተቀበለና በዛም የሚያምን መሆንን፣ ችሎታንና ሕዝባዊነትን፣አገር ወዳድነትን ይጠይቃል።በሁለተኛው የስልጣን አወጣጥ ግን ሃይልን፣ማንአለብኝነትን፣የተከተለ ጭካኔን ብቻ የሚጠይቅ ነው።በመሆኑም አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ ተብለው ይጠራሉ ወይም ይመደባሉ።፣
አገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት በሁለተኛው ዓይነት በስልጣን ላይ በተቀመጡ አምባገነኖች በሚከተሉትና በሚያሰፍኑት ስርዓት ስር ስትማቅቅ የኖረች አሁንም እየማቀቀች የምትገኝ አገር ነች።ሌሎቹም የቅርብና የሩቅ የጎረቤት አገሮች እንደዚሁ በአምባገነን በሆኑ በተመሳሳይ ዓይነት ስርዓቶች ስር የሚማቅቁ ናቸው።
የአምባገነን መንግሥት ወይም ስርዓት የስልጣን ዘይቤ አመጽና ጦርነትን መሰረት ያደረገ ነው። በዚህ አስተሳሰብ የተለከፉት በጦርነትና በሃይል ስልጣን ይይዛሉ፣በጦርነትና በሃይልም የስልጣን ዕድሜያቸውን ያራዝማሉ።ለእነሱ ሰላምና የሕዝብ መረጋጋት አጥፊያቸው ነው።ሰላም የማይኖርበትን መንገድ ይፈጥራሉ፤ሁል ጊዜ ሕዝብ በስጋትና በፍርሃት እያደረ ወደ እነሱ አጥፊ ስርዓት ፊቱን እንዳያዞርና የትግል ስሜቱ እንዲኮላሽ ያደርጋሉ።ከነዚህም ዋናውና አንዱ ስልታቸው በአገር ውስጥና በጎረቤት አገር ሽብርና ጦርነት የሚነሳበትን መንገድ መፍጠርና “አገርህ በውጭ ወራሪ ሃይል ተከበበች ወይም ተወረረች” የሚለው የክተት ጥሪ ማወጅ ይሆናል።በራሳቸው አናት ላይ ያለውን ሸክምና አደጋ በሕዝቡ ትከሻ ላይ ለመወርወርና ትኩረቱን ለመቀየር የማይገለብጡት ድንጋይ የለም።ይህን የጥፋት መልእክት የሚቃወሙትን በመግደል፣እምቢ ያሉትን አፍሶ በማስገደድ የጦር ሜዳ ጭዳ ያደርጉታል።ስልጣን ሲይዙ የሕዝቡን ደም በማፍሰስ እንደሆነው ሁሉ በሥልጣንም ላይ ለመቆየት እንዲሁ ሕዝብ ደሙን እንዲያፈስላቸው በማስገደድና በማታለል ሰፊ ዘመቻና ዝግጅት ያደርጋሉ።በጦርነቱም ጊዜ ሆነ ማግስት ለሕዝቡ የሚተርፈው ነገር ቢኖር ፣በጦር ሜዳ መሞት፣መቁሰል፣አካለጎደሎ መሆን፣ የንብረት መውደም፣መፈናቀል፣ በስንቅና ትጥቅ የግልና የአገሪቱን ሃብት ማባከን ነው። ከዚያም በላይ ጦርነቱ ሲያልቅ በሕዝብ መካከል የማይከስም የእርስ በርስ ጥላቻና ቋሚ ጠላትነት መፍጠር ይሆናል።
የሰሞኑም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተከሰተ የተባለው ግጭት በሥልጣን ላይ የተቀመጡት ሁለት አምባገነኖች የሚጫወቱት የዚሁ የሥልጣን አድን ቲያትር ውጤት ነው።ያለፈውም ሆነ በየጊዜው የሚነሳው ውጥረትና ግጭት የወያኔና የሻእብያ የጥቅም ግጭት እንጂ የሕዝብ ግጭት አይደለም።ሁለቱም አምባገነን ሥርአቶች በሕዝብ የተጠሉ ናቸው፡፤ሁለቱም መንግሥት ነን ባይ ቡድኖች እጃቸው በንጹሃን ደም የጨቀዬ ነው።በሁለቱም ስርዓቶች ስር የሚኖረው ሕዝብ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ የሚያደርገው ትግል እያደገ በመሄድ ላይ ነው።ይህንን ሕዝባዊ አመጽና ትግል ለማፈንና ለማቀዝቀዝ ያላቸው አንዱና ቀሪው መሳሪያ “አገርህ ተወረረች” በሚል ጩኸት ማደናገርና በእነሱ ላይ ያነጣጠረውን ፍልሚያ ለጊዜው እንዲረሳና ወደ አላስፈላጊ ጦርነት ገብቶ እርስ በርሱ እንዲተላለቅ ማድረግ ነው።የዚህ አይነቱ ስልት የዛሬ አስራ ስድስት ዓመት የተጠቀሙበት ሲሆን የብዙ መቶ ሽህ ንጹሃን ደምና የአገር ሃብትና ቅርስ ወድሞ እስከ አሁንም በሥልጣን ላይ ለመቆየት እረድቷቸዋል።የሰሞኑም  ተንኳሽ  ግጭት  ከዚያ  የተለየ  አይደለም።ያለፈው  ጦርነት  ለሕዝብ  አለመተማመንና  መራራቅ
 
እንዳገለገለ ሁሉ ያሁኑም በሁለቱም ተንኳሽነት የሚካሄደው ግጭት ወደ ከፍተኛ ጦርነት ቢያመራ ከሚያደርሰው የሕይወትና የሃብት ጥፋት በላይ ከዚያ ለከፋ ለከባቢ ቀውስና ለሕዝብ ቋሚ ጠላትነት የሚዳርግ ይሆናል።
ህወሃት/ኢሕአዴግ ባለፈው ጊዜ ከሻእቢያ ጋር ባደረገው ጦርነት የኢትዮጵያን መብት፣ ክብርና ዳር ድንበር እንዳላስጠበቀና እንደውም ጎጂ በሆነ ውልና መደራደር የአገራችንን ጥቅም አሳልፎ የሰጠ፣የአገር ክህደት የፈጸመ፣ ለውጭ ሃይሎች ጣልቃ መግባትና በሰላም ፈላጊነት ሽፋን ከመጠቀም ሌላ ያመጣው ጥቅም የለም።አሁንም የዚህ የጦርነት አዝማሚያ ለቀጣይ የሁለት አምባገነኖች እርቅና ድርድር መንደርደሪያ ሊሆን ይችላል።ከድርድር በዃላም የሚገኘው ውጤት የኢትዮጵያን ህልውናና ታሪካዊ መብት የሚያፈርስና አሳልፎ የሚሰጥ እንጂ የሚያረጋግጥና የሚያስከብር አይሆንም።በኤርትራ የሰፈነው ሥርዓትና መንግስት ለኢትዮጵያ ቅንጣት ያህል አይጨነቅም፤ሙሉ ለሙሉ ተበታትናና ተዳክማ ብትኖር ፍላጎቱ ነው።ጠንካራ ኢትዮጵያ፣አንድነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያ፣ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያ ለእሱ መኖር አደጋ ነው።ለጊዜው ከህወሃት መራሹ ኢሕአዴግ የተጣላ ቢመስልም፣እንደ ህወሃት መራሹ ቡድን ሊያገለግለው የሚችል ሌላ ቡድን ካልፈጠረ በስተቀር ኢትዮጵያን በማፈራረሱ ደረጃ ከወያኔ የተሻለ አጋር ሊኖረው እንደማይችል ያውቀዋል። ህወሃት/ኢሕአዴግም እንደዚሁ።የአሁኑም እሰጥ አገባ የሁለት ወዳጆች ጊዜያዊ ጠብ ነው።አህያ ላህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም!!እንዲሉ።ይህን ሁሉ ስናገናዝብ ጦርነቱ የሕዝብን ጥቅም የሚያስከብር ሳይሆን አምባገነኖች ለሥልጣናቸው መራዘም የሚገለገሉበት መሣሪያ ሆኖ እናገኘዋለን።
ሕዝብ በሰላምና በመቀራረብ፣ ሊኖር የሚችለው ጦር ሰባቂ የሆኑ አምባገነን ሃይሎችና መንግሥታት ሲወገዱና በዴሞክራሲ ስርዓት ሲተኩ ብቻ ነው።ለዚያ ደግሞ በአምባገነኖች የሚጎሸመውን የጦርነት ነጋሪትና አዋጅ ሳይቀበሉ ተባብረው የጋራ ጠላታቸው የሆኑትን የአምባገነን ስርዓቶች ለማሶገድ ሲነሱ ነው።የሻእቢያን ስርዓት የሚቃወሙም ሆነ የህወሃት/ኢሕአዴግን የሚቃወሙ ማወቅ የሚገባቸው አንዱን አምባገነን ተጠግቶ ሌላውን አምባገነን ማሶገድ እንደማይቻል ነው። የሚታገሉት ለዴሞክራሲ ስርዓት ከሆነ እነዚህ በስልጣን ላይ ያሉት አምባገነኖች ጠላቶቻቸው ናቸው ።የትም ይሁን የትም አምባገነን አምባገነን ነው፡፤ለዲሞክራሲ የቆመ ሃይል ከሁለት አንዱን አይመርጥም።”ከጅንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል” ነው።ጅንጀሮ ጅንጀሮ ነው አምባገነንም አምባገነን!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ)አሁን በኤርትራና በቀረው ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተቀመጡት ሁለት አምባገነን ቡድኖች የቀውስና የጦርነት ተጠያቂዎች እንደሆኑ ያምናል፡፤ሕዝብ እነዚህ ጦረኛ፣አምባገነንና ዘራፊ ቡድኖች ለዘረጉት የዕድሜ አርዝም የጦርነት ጥሪ ጆሮውን እንዳይሰጥ፣ደሙን እንዳያፈስ እያሳሰበ ብሎም ሃይሉን አስተባብሮ እነዚህን አምባገነኖች ለማሶገድና በሰላም ለመኖር የሚችልበትን መንገድ እንዲፈጥር ተባብሮ እንዲነሳ ጥሪ ያደርጋል።ሻእቢያና ህወሃት መራሹ ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ የኢትዮጵያና የኤርትራ ኑዋሪ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የከባቢው ሕዝብ በሰላም አይኖርም።
በጦርነት ሰበብ አድርጎ ድርድር በመክፈት የአገርን ጥቅምና መሬት አሳልፎ ለመስጠት የሚደረገውን የብልጦች አስመሳይ እሩጫና ዝግጅት ሁሉም ሊያውቀውና ሊታገለው ይገባል። በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ፣ለአገራቸው ጥቅም እንቆማለን የሚሉ የገዝው ቡድን ደጋፊወች ጭምር ከሌላው አገር ወዳድ ጋር ተባብረው በስማቸው የሚፈጸመውን ክህደትና አገር ጎጂ ተግባር ሊቃወሙት ይገባል። ያለፈው ይብቃ !ብለው መነሳት ይጠበቅባቸዋል።
በውጭ የሚኖረውም ዜጋ ጦርነቱን እንዲያወግዝና ሁለቱም አምባገነን ስርዓቶች እንዲወገዱ በጋራ እንዲታገል ጥሪያችንን አሁንም እናቀርባለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ)