የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ [ሸንጎ] ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ

home

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ አመራር ምክር ቤት የተሳካ ጉባኤ አካሄደ

በቅርቡ የሽንጎው ከፍተኛ አመራር አካል የሆነው ምክር ቤት ባካሄደው የሁለት ቀን ስብሰባ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ሁኔታ በሰፊው መርምሮ ለቀጣዩም ትግል ምን መደረግ እንዳለበት መመሪያ በመሰጠት ተጠናቋል።

በተጨማሪም የሽንጎው የተለያዩ የስራ ክፍሎች የስራ አፈጻጸምን በተመለከተ የቀረቡለትን ሪፖርቶች መርምሮ ትግሉ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን ተጨማሪ መመሪያ በመስጠት ተጠናቋል። በተለይም ደግሞ ሽንጎው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያካሂደው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ የተገኙትን መልካም ግንኙነተቶችን እና አበረታች ውጤቶች ከመረመረ በኋላ በዚህ መስክ የሚካሄደው እንቅስቃሴ እጅግ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መመሪያ ሰጥቷል፡

የሸንጎው ምክር ቤት የኢትዮጵያን አጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታ የገመገመ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ውስጥ እጅግ ተጠናከሮ የቀጠለውን ሁለንተናዊ የመብት ረገጣ ፣ በተለይም ደግሞ ባሁኑ ሰአት ዜጎች መሰረታዊ የሆነውን መሪዎቻቸውን በድምጻቸው በነጻነት የመመምረጥ መብታቸውን በትክክል እንዳይገልጹ ገዥው ሕወሀት/ኢህአዴግ እና እንደልቡ የሚያዛቸው የምርጫ የጸጥታና የፍትህ ተቋማት በህዝባችን ላይ በቀጣይነት እያሳዩት ያለውን እጅግ አሳዛኛ ግፍ ባፅጽንኦና በታላቅ ሀዘን ተገንዛቧል።

በዚህ እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ፣ የፖለቲካ መድረኩን ለገዥው ቡድን ባለመተው የህዝባችንን መብት ለማስከበር እጅግ ብዙ መስዋእትነት ለከፈሉ እና በመክፈል ላይ ለሚገኙ ታጋዮች ሁሉ ያለውን አድናቆት አክብሮትና የትግል አንድነት ምክር ቤቱ በድጋሜ አረጋግጧል።

ገዥው ቡድን ህወሓት/ኢህአዴግ የህዝባችንን መብት በሁሉም መልኩ መርገጡን በቀጠለ ቁጥር ህዝባችን ደግሞ በስርዓቱ ላይ ያለው ብሶት፣ ቅሬታና ጥላቻ እጅግ እየሰፋ መምጣቱን፣ የሚደርስበት ግፍ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ እንደሆነም ብዙ መረጃዎችን ምክር ቤቱ ተመልክቷል። ዛሬ ህዝባችን ከዚህ ስርዓት መልካም ነገርን መጠበቅ ትቷል። በራሱ አነሳሽነት ስርአቱ እንዲወገድለት አምርሮ ይፈልጋል። አልገዛም ማለትን በየቦታው እያሳየ ነው። ለመብቱ መቆሙን በግልጽ ማሳየቱን ቀጥሏል። የፍርሀት ድባብን አፈራርሶ በመጣል ላይ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪም በገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ የርስበርስ አለመተማመንና ውጥረትም እየሰፋ መምጣቱን የሽንጎው ከፍተኛ አመራር ምክር ቤት በሰፊው ቃኝቷል።

እነዚህን ሁሉ ባንድ ላይ ስንመለከትም ሀገሪቱ ውስጥ ህዝባዊ የለውጥ አመጽ ሊነሳ የሚችልበት ሁኔታ እጅግ በፍጥነት እየተቃረበ መሆኑን ሽንጎው ተገንዝቧል።
ገዥው ቡድን ከላይ ሲታይ ሁኔታዎችን የተቆጣጠረና የተረጋጋ ይምሰል እንጂ ከሁሉም ህዝብ፣ ከሁሉም ፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማህበራት የሀይማኖት ተቋሞች ጋር የገባበት ቅራኔ የራሱን ጥላ ሳይቀር ማንንም እንዳያምን ስላደረገው እነሆ ሌትም ቀንም በመደናበር፣ ከአንዱ ስህተት ወደሌላው እየተላተመ ወደ መጨረሻው መቃብሩ እንደተቃረበ እንረዳለን።

ሀላፊነት የጎደለው ይህ ጠባብ ቡድን፣ ከራሱ ስልጣን እና አልጠግብ ባይ ዝርፊያ ባሻገር ለማገናዘብ ባለመቻሉም ሀገሪቱን ራሷን ወደ አደጋ አፋፍ አድርሷታል።

ይህን ሀገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ የሚከታተሉ የሀገሪቱ ጠላቶችም የህዝባችንን የለውጥ እንቅስቃሴ ለአደጋና ለራሳቸው ቀጣይ አጥፊ አጀንዳ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ሸንጎ ተገንዝቧል።

ሀገራችንና ህዝባችን ከታሰሩበት የግፍ ሰንሰለት ነጻ ለማውጣትና በምትኩም አንድነቷ በተጠበቀ ኢትዮጳያ ስር ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲአዊ ስርአትን ለመገንባት የሚደረገው ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሽንጎው ምክር ቤት መመሪያ የሰጠ ሲሆን፣ ይህን ትግል ወደግብ ለማድረስም ሆነ ከላይ የጠቀስናቸውን አሳሳቢ ሁኔታዎች ለማስወገድ ያንድነት ሀይሎች ከምን ጊዜውም በላይ በመተባበር በንቃት እንዲንቀሳቀሱ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
 ሀገራችን ከምትገኝበት አስከፊ ሁኔታ ሁሉም አሽናፊና ተጠቃሚ ወደሆነበት ስርአት ለመሽጋገር ብሄራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ አማራጭ የሌለው እንደሆነ ምክርቤቱ አጽንኦ ሰጥቷል።

የሸንጎው ያመራር ምክር ቤት ዛሬ በሚካሄደው ትግል ውስጥ ያማራጭ  መገናኛ ብዙሃንን አስፈልጊነት በሰፊው ከተወያየ በኋላ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፍ ያጭር ሞገድ ሬዲዮ ፕሮግራም ባስቸኳይ እንደሚያስፈልግና፣ ይህን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ እና ጊዜያቸውን በማበርከት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ